“ከሎዛ የተማርኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ” ረድኤት አስረሳኸኝ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ከኢትዮጵያ የ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ድል በኋላ የወቅቱ ድንቅ አጥቂዎች ረድኤት አስረሳኸኝ እና ሎዛ አበራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ታሪክን እየፃፉ ይገኛሉ ፤ ከከምባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ የተወለዱት ሁለቱ እንስት እግር ኳስ ተጫዋቾች ሎዛ አበራ እና ረድኤት አስረሳኸኝ። በርካቶቻችን የሎዛ አበራን የእግር ኳስ ህይወት እና ስኬት በደንብ የምናውቅ ቢሆንም ሎዛ አበራን ምሳሌ በማድረግ ብቅ ያላችው እና በ2008 ለደቡብ ክልል ስትጫወት የነበረችው ረድኤት ትልቅ ተጫዋች የመሆን የሎዛ መንገድ ላይ ናት። ተጫዋቿ በአሁኑ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የደደቢት የአሰልጣኝነት ዘመን ቡድኑን በመቀላቀል የክለብ ህይወቷን የጀመረች ሲሆን በመቀጠል ሲዳማ ቡና ፣ ጌዲኦ ዲላ እና ዓምና ደግሞ ሀዋሳ ከተማን በመቀላቀል ዕድገቷን አስቀጥላለች።

በትውልድ መንደሯ ዱራሜ የበቀለችውን የቀድሞዋ የሀዋሳ ፣ ደደቢት ፣ አዳማ ፣ ቢርኪርካራ እና በአሁኑ ሰዓት በንግድ ባንክ እየተጫወተች ያለችውን በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ላይ ስሟ ጎልቶ የሚነሳው ሎዛ አበራን እያያች ያደገችው ረድኤት አስረሳኸኝ በሴካፋ ዋንጫ ያሳየችው መልካም አቋም የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ እስከ አምስተኛው ዙር ድረስ ሲጓዝ ረድኤት 

ለሀገሯ ጎሎችን በማቆጠር ትልቅ ድርሻ እየተወጣች ነው። ተጫዋቿ በመጨረሻው የታንዛኒያ ጨዋታ ላይ ሁለት ጎሎችን ከመረብ በማገናኘት የሎዛ አበራን የግብ ሪከርድ በአንድ በማሻሻል ሰባት አድርሰዋለች። ከዚህ ጋር በተያያዘ ረድኤት የተሰማትን ስሜት እና ተያያዥ ጥያቄዎች ከሎዛ አበራ ጋር አጣምረን በተከታዩ መልክ አቅርበንላችኋል፡፡

“ከዚህ በኋላ ብዙ መስራት እንዳለብኝ እረዳለሁ” ረድኤት አስረሳኸኝ 

ስለ ታንዛኒያው ጨዋታ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር ። እኛ  ተሸንፈን ስለመጣን አንድ እና አንድ ማሸነፉን በጣም እንፈልገው ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ ያገኛናቸውን የጎል ዕድሎች አልተጠቀምንም ነበር ፤ ፍፁም ቅጣት ምትም ስተናል። ግን አሸንፈን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነበርን። ከዕረፍት በኋላ ድክመቶቻችንን አስተካክለን ማሸነፍ ችለናል።

ፍፁም ቅጣት ምት ስለመሳቷ

“ፍፁም ቅጣት ምቱን እስተዋለው ብዬ አላሰብኩም። ግን ከዛ በኋላ እንደማገባ እርግጠኛ ነበርኩ። አሰልጣኝ ፍሬው በዕረፍት ሰዓት ደጋግሞ ይነግረኝ ነበር። በራስ መተማመኔን ከፍ አድርጎት ወሳኙን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሬያለው።

ስለቀጣዩ የመጨረሻ የማጣሪያ ወሳኝ ጨዋታ 

“ቅድሚያ ለፈጣሪ ሁሉን ነገር መስጠት ነው። ከዚህ በኋላ በሉት ቀናቶች ያሉብን ጉድለቶች ላይ ሰርተን  ከጋና ለሚኖረው ጨዋታ በቂ የሆነ ዝግጅት እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ።

ከሎዛ ስለወሰደችው ትምህርት እና ስለግንኙነታቸው

“ከሎዛ የተማርኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሎዛ ጠንካራ ሴት ናት ፤ በህይወቷም ፣ በዕምነቷም በሥራዋም ጎበዝ ናት። በጣም ታታሪ ፣ ሙያዋን የምታከብር ተምሳሌት የሆነች ልጅ ናት። እኔም እርሷን በማየት ራሴን በትልቅ ደረጃ ለማሳደግ ከእርሷ ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ። ሁሌም ቢሆን ጨዋታ ሲኖረን በመደወል በአንዳንድ ነገሮች ትመክረኛለች። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ትነግረኛለች ፤ ታበረታታኛለች። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት እፈልጋለሁ።

ዱራሜ ለሴት ተጫዋቾች ስለሚሰጠው የተለየ ሚስጥር

“የተለየ ሚስጢር የለውም። እኛ ወጥተን እንታይ እንጂ በጣም አቅም ያላቸው እንዳኛ ወጥተው መጫወት ያልቻሉ ብዙ ሴቶች አሉ። አሁን አሁን በቂ ባይሆንም በዱራሜ ለሴቶች እግርኳስ ትኩረት እየተሰጠ ነው። በጣም መናገር የምፈልገው መታየት ቢችሉ ዕድሉን ቢያገኙ ከእኛ በላይ ወጥተው መጫወት የሚችሉ ብዙ እህቶች አሉ፡፡

በሎዛ አበራ ተይዞ የነበረውን የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከፍተኛ የጎል መጠን ስለማሻሻሏ

“ይህ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁንም  ካስቆጠርኩት ጎል በበለጠ ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር የበለጠ የማሻሻል ሀሳቡ አለኝ ፤ ለዚህም ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡

ስለ ቀጣይ ዕቅዷ

“ከዚህ በኋላ ብዙ መስራት እንዳለብኝ በዙ ነገር እንደሚቀረኝ ነው የማስበው። በቀጣይ ላለው ወሳኝ የዓለም ዋንጫ ማጣርያም ጨዋታ በማለፍ በኮሳትሪካ መገኘትን አስባለሁ። ለዚህም ራሴን አዘጋጅቼ የበለጠ በመስራት አቅሜን በትልቅ ደረጃ ማሳየት እፈልጋለው።”

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጧ አጥቂ እንደምትሆን አስባለሁ” ሎዛ አበራ

ከረድኤት ጋር ስላላቸው ግንኙነት

“ከረድኤት ጋር በቤተሰብም ደረጃ እንተዋወቃለን ዝምድናም አለን። ወደ እግርኳሱ ስመጣ ከእኔ በኋላ እኔ እሰራበት ከነበረው ፕሮጀክት ነው የወጣችው። ያው በየጊዜው አቅሟ ከፍ እያለ ችሎታዋ እያደገ ማንነቷን እያሳየች የመጣች ልጅ ናት። በዚህ ወሳኝ ቀን ደግሞ ሁለት ግቦችን በማግባቷ ደስ ብሎኛል። ደውዬላትም ደስታዬን ገልጬላታለሁ። በዚህ መቆም እንደሌለባት እና ብዙ ነገር ከፊቷ እንደሚጠብቃት ትልቅ ደረጃም እንደምትደርስ ነግሬያታለሁ። አንድ አጥቂ ሊኖረው የሚችለው ጥራት እሷ ውስጥ አለ። ነገ ከኛ በተሻለ ትልቅ ደረጃ ደርሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጧ አጥቂ እንደምትሆን አስባለሁ ፤ እናም ደግሞ አምናለሁ።

በዱራሜ ሴቶች እግርኳስ ላይ ስላለው አሁናዊ ትኩረት

“ያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እየመጣ ነው ብዬ አስባለው። ከበፊትም ጀምሮ የሚጫወቱ የኛ ሲኒየሮች አሉ። ለምሳሌ አሁን ኤልፓ ምትጫወተው ምንትዋብ ዮሐንስ ከእኔ ሲኒየር ነች። እነሱ በነበሩበት ጊዜ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ብዙ የጨዋታ ዕድል አለማግኘት እና ያለ መሳተፍ ነበር። ከዛ በኋላ እኔ ከመጣሁበት ሰዓት ጀምሮ በዞኑ ፕሮጀክቶች መኖራቸው እና በተለይ የኔ መውጣት ከዛም ደግሞ አልፎ ጥሩ ደረጃ መድረስ ‘ልጆቻችን እንደሷ መሆን ይችላሉ’ ብለው በማሰብ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሜዳ መላክ ችለዋል። አሁን በርግጥ ከጊዜ ወደጊዜ የተሻሻለ የመጣ ነገር ስላለ በብዙ ፍላጎት ችሎታ ያላቸው ልጆች እየወጡ ነው።

ረድኤት ዓለም ዋንጫ ማጣርያ የጎል መጠኑን ስልማሻሻሏ

“በጣም ደስ ብሎኛል። ድጋሚ ቀሪ ማጣሪያም ስላለ ተጨማሪ ጎሎችን ታገባለች ብዬ አስባለው። አንድ ነገር ባለበት መቆም የለበትም ፤ የሚያስቀጥል ሰው ያስፈልጋል። እኔ በዘመኔ የሰራሁትን አንድ ታሪክ እሷ ደግሞ በእርሷ ዘመን ሌላ ታሪክ ስላስቀጠለች በጣም ደስ ብሎኛል። በዚህ መልኩ አንድ ትውልድ ሲመጣ እና አዲስ ነገር ሲያመጣ የእኛም እግርኳስ ስለሚያድግ በዛ ውስጥ እንዳለ ሰው በጣም ደስተኛ ነኝ። እንደዚህ ዓይነት ትውልድም በመፈጠሩ በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ። እሷም ከዚህ በኋላም ለዓለም ዋንጫ አልፋ ሌላ ስኬት እንደሚኖራት እርግጠኛ ነኝ፡፡”