ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ዓበይት አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በሦስተኛው የፅሁፋችን ክፍል ተዳሰዋል።

👉 በወጣቶች የፀና ዕምነት ያላቸው ዮሐንስ ሳህሌ

ከአሜሪካ መልስ በኢትዮጵያ እግርኳስ በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለቦች በነበራቸው ቆይታ በወጣቶች ላይ የፀና ዕምነት እንዳላቸው እያስመሰከሩ የሚገኙት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ይህን ሂደት በመከላከያም ዳግም እያስመለከቱን ይገኛል።

ቢኒያም በላይ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ዕምነት አሳድረው ከፍ ባለው የፉክክር እግርኳስ ውስጥ እንዲታዩ በር የከፈቱት አሰልጣኙ በመከላከያ ቤት ደግሞ ቀጣዮቹን ኮከቦች ከወዲሁ እያሳዩን ያለ ይመስላል።

በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ከጥቂት ባለልምድ ተጫዋቾች ጋር በማጣመር በተገነባው የመከላከያ ስብስብ ውስጥ አዳዲስ ወጣት ተጫዋቾችን እያስተዋወቁን ይገኛል።

ግሩም ሀጎስ ፣ አቤል ነጋሽ ፣ ተሾመ በላቸው ፣ ኢብራሂም ሁሴን በተለይ ለፕሪሚየር ሊጉ አዳዲስ ስሞች ሲሆኑ ሠመረ ሃፍታይ ፣ ብሩክ ሰሙ ፣ ገናናው ረጋሳ ዓይነት ተጫዋቾች ደግሞ ከአሰልጣኙ ጋር ከዚህ ቀደም በጋራ የመስራት ልምድ ቢኖራቸውም ገና የእግርኳስ ህይወታቸው ጅማሮ ላይ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

አሰልጣኙ ወጣት ተጫዋቾች በጨዋታ ደቂቃዎች እንዲማሩ እና ይበልጥ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ የሚሰጡት ዕድል ሌሎች የሊጉ አሰልጣኞች ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ነው።

አሰልጣኙ ከዚህ ሳምንቱ ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል ፤

“ምንም ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን አሰልፈናል። ተሾመ ከ20 ዓመት በታች የተገኘ ተጫዋች ነው። ፕሪሚየር ሊግ ሲጫወትም የመጀመርያው ነው። እንደነዚህ ያሉ ልጆችን ይዘን ነው የምንጫወተው። በሌላ መንገድ ዕድል እየሰጠሀቸው ነው። ዕድሉን ደግሞ መጠቀም አለባቸው። ተሾመ ከእኛ ጋር ከቆየ ገና ሁለት ወሩ ነው። አንድ ያለን የወታደር ተጫዋች ነው ፤ ሌሎቹንም ያበረታታል ብለን እናስባለን። የሚጫወተው ገና በታዳጊነት ሲሆን አረንጓዴ ካርድ ያልወጣለት ነው። ስለዚህ በአንድ ቀን ገብቶ ጫና ባለበት ውድድር ላይ ኃለፊነቱን መወጣቱ በጣም የሚመሰገን ነው።

“እንግዲህ ልጆቹ ላይ ሜዳ ላይ ያለውን ነገር የምንተወው ከሜዳ ውጭ ያለውን ስራው ደግሞ እኛ እንወጣለን። የጨዋታውን ሂደት ደግሞ እንደነዚህ ያሉ ልጆች እየገቡ ለምሳሌ ግሩም ፣ ብሩክ እና ኢብራሂም ከ23 ዓመት በታች ወጣት ልጅ ናቸው። እነዚህን ይዘን ልምድ እየያዙ ሲመጡ በተሻለ ኳስ ይጫወታሉ ይሄን ለማስቀጠል ነው የምናስበው።” ሲሉ ተደምጠዋል።

👉 ህመም ያስተናገዱት ጳውሎስ ጌታቸው

ወልቂጤ ከተማ ከመከላከያ ባደረጉት ጨዋታ ከህመማቸው እየተጋሉ ጨዋታውን ለመመምራት ሜዳ የተገኙት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ህመማቸው አገርሽቶባቸው በአምቡላንስ ወደ ክሊኒክ ለመወሰድ ተገደዋል።

ከዚህ ቀደም በ2011 የውድድር ዘመን የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ቡድናቸው በባህር ዳር ዓለምዓቀፍ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 በረታበት ጨዋታ እንዲሁ በጨዋታ ወቅት የጤና ዕክል አጋጥሟቸው ከስታዲየም ወደ ህክምና ተቋም ማምራታቸው አይዘነጋም።

አሰልጣኙ በህመም ምክንያት አለመኖራቸውን ተከትሎ ምክትላቸው የሆኑት አሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድኑን ሲመሩ የተመለከትን ሲሆን ውጤቱ ግን በቃራኒው ወደ መከላከያ አድልቶ ጨዋታው ተጠናቋል።

ምክትላቸው የሆኑት እዮብ ማለም ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ድህረ ጨዋታ አስተያየት ላይ ዋና አሰልጣኙ አለመኖራቸው በሥነልቦና ረገድ ስለፈጠረባቸው ጫና ያነሱ ሲሆን ይህም የፈጠረው ድንጋጤ ውጤት እንዳሳጣቸው ጠቁመዋል።

👉ጫና ውስጥ የሚገኙት ዘላለም ሽፈራው

ሰበታ ከተማ ቀስ በቀስ ወደ ሊጉ ግርጌ እየተንደረደረ ይመስላል ፤ ጅማ አባ ጅፋር ሰሞነኛ መነቃቃት እና የሰበታ ከተማ እየተንሸተተ መገኘት ሰበታን ይበልጥ ጫና ውስጥ እየከተተው ይገኛል።

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው ቡድኑ አሰልጣኙ የሚታወቁበት የመከላከል ጨዋታን እንኳን በወጉ ለመከወን እየተቸገረ ይገኛል። ከጨዋታ ጨዋታም ቡድኑ በቀላሉ ግቦች የሚቆጠሩበት አልፍ ሲልም በማጥቃቱ ወቅት ዕድሎችን ለመፍጠር አብዝቶ የሚቸገር ቡድን ሆኖ እየተመለከትነው እንገኛለን።

አሰልጣኙም በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ይህን ነገር ለማሻሻል እየጣሩ ቢሆንም ከመሻሻል ከመፈለግ ባለፈ ሜዳ ላይ በሚታይ ደረጃ ቡድናቸው ይህን ነገር በተግባር ለመቅረፍ እየተቸገረ ስለመሆኑ ሲናገሩ ይደመጣል።

ታድያ አሁን ባለው ሁኔታ አሰልጣኙ ከጨዋታ ጨዋታ ጫና እየበረታባቸው ይገኛል። በመሆኑም ቡድኑ እሳቸው ላይ ዕምነቱ ሳይሟጠጥ ይህን ሁኔታ ይቀለበሳል ብሎ ይታገሳቸዋል ወይንስ እንደ አብዛኞቹ ክለቦች በአሰልጣኝ ለውጥ ሁኔታውን ለማስተካከል ይጥራል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉የዘርዓይ ሙሉ አስተያየት

በሊጋችን በተለይ የመጫወቻ ሜዳዎችን እና ዳኝነትን በተመለከተ አሰልጣኞች በመልካም ጎኑ የሚነሱ አስተያየቶችን ሲሰጡ አይስተዋልም።

በዚህ ረገድ ግን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በመልካምነት የሚጠቀስ ሀሳብ በዚህኛው ሳምንት ሲሰጡ ተደምጠዋል። አሰልጣኙ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የድሬዳዋ ዓለምዓቀፍ ስታዲየም በተመለከተ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“የኛ ቡድን ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። እውነት ለመናገር ሜዳው ምቹ ነው። ሀዋሳ ላይ ሜዳው ምቹ ስላልሆነ የምናገኛቸውን ኳሶች አንጠቀምም ነበር። እዚህ ሜዳ ላይ ጎሎች ይገባሉ። የሜዳው ተፅዕኖ አለው ብዬ አስባለው። ከጨዋታ ጨዋታ ልጆቼ ራሳቸውን እያሳደጉ ስለመጡ በተሻለ እንገፋበታለን ብዬ አስባለው።”