ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች በመጨረሻው ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉በሲዳማ ቡና ነገሮች መልክ እየያዙ ይመስላል

በከፍተኛ ተስፋ ውድድሩን ቢጀምርም በሚጠበቀው ልክ ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት የነበረው ሲዳማ ቡና በተለይ በ7ኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ 4-0 በተረታበት ጨዋታ ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ እዚህ እዛም ይሰሙ የነበሩ የተቃውሞ ድምፆች አይለው ወደ ፊት የመጡበት ወቅት እንደነበር አይዘነጋም።

ታድያ በዚያ ጨዋታ ወቅት የቡድኑ አባላት በተለይም አሰልጣኙ ላይ ያነጣጠረ የነበረው ተቃውሞ በጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲከሰቱ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ አክሲዮን ማህበሩ የገንዘብ እንዲሁም በቀጣይ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታ ያለ ደጋፊ እንዲጫወት ብይን መስጠቱ አይዘነጋም።

በመሆኑም የ3 ጨዋታ ቅጣታቸውን አጠናቀው በዚህኛው ሳምንት ቡድናቸው ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ሲጫወት ወደ ሜዳ የተመለሱት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በማህበራቸው አማካኝነት በድርጊታቸው “ያስከፏቸውን” (አሰልጣኙን ፣ ተጫዋቾቹን እና የክለቡን አመራር) በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ክለቡ ባረፈበት ሆቴል ደጋፊዎች ባነር አሰርተው በመሄድ በይፋ የቡድኑን አባላት ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን በስታዲየም የተለያየ ይዘት ያላቸው ፅሁፉችን ይዘው ከክለባቸው አባላት ባለፈ የሊግ አክሲዮን ማህበሩን እና የእግርኳስ ፌደሬሹኑን እንዲሁ ይቅርታ ጠይቀዋል።

በመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ የተለያየው ቡድን በሂደት በውጤት ረገድ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። ከደጋፊዎቹ ጋር የነበረው ውጥረት በዚህ መልኩ መለዘብ መጀመሩ ደግሞ አጠቃላይ የቡድኑን መንፈስ ከመለወጥ ባለፈ አሰልጣኙ ተረጋግተው ስራቸው እንዲሰሩ የሚረዳ ሲሆን ይህም በቀጣይ የክለቡ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በዚህ መልኩ ባይሆንም በተመሳሳይ በያዝነው የውድድር ዘመን የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎችም እንዲሁ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ በተወሰነ መልኩ ከክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ቡድን ጋር ልዩነቶች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት በደጋፊዎቹ በተደረገ ጥረት በሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች የሚታይ ለውጥ እየተመለከትን እንገኛለን።

👉 የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች…

ከ10ኛ የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ ሊጉን በማስተናገድ ላይ የሚገኙት ድሬዎች ቡድናቸውን በቁጥር በርከት ብለው እያበረታቱ ይገኛል።

በ10ኛ ሳምንት መከላከያን 1-0 ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የሆኑት አቶ ከድር ጆሃር የከተማው ነዋሪ በቀጣይ ጨዋታዎች በቁጥር በርከት ብሎ ቡድኑን እንዲያበረታታ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ በሀዋሳ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ቢሸነፍም በጣም በርካታ የከተማው ነዋሪ ስታድየም በመገኘት ቡድኑን ደግፏል።

ከተማው እየተደረገ በሚገኘው ውድድር በተቻለ መጠን ነጥቦችን የመሰብሰብ ፍላጎት እንዳለው በግልፅ የሚታየው ድሬዳዋ በቀድሞው ቴክኒክ ዳይሬክተር ፉአድ የሱፍ እየተመራ መነቃቃት ላይ ይገኛል። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከሚተችበት በተቃራኒ በተሻለ ቁጥር ከአካባቢው የተገኙ ተጫዋቾች እየተጠቀመ መገኘቱ ከደጋፊዎች ጋር ይበልጥ በስሜት እንዲተሳሰር እየረዳው ይገኛል።

በመጀመሪያ ዙር ተደጋጋሚ ነጥቦችን በመጣል ባለፉት ዓመታት በሁለተኛው ዙር ላለመውረድ ሲታገል የሚስተዋለው ድሬዳዋ ከተማ ውድድሩ በዚህ ወቅት ወደ ከተማው መምጣቱ በደጋፊቹ ታግዞ በተሻለ ነጥቦችን በመሰብሰብ የተሻለ የውድድር ዘመን እንዲያሳልፍ ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ታምሩ ባልቻ የተዘከረበት ጨዋታ

በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው ወጣቱ አጥቂ ታምሩ ባልቻ የትውልድ ቦታው ክለብ በሆነው ሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ተዘክሯል።

ሰበታ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ካደረጉት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የሰበታ ከተማ እግርኳስ ክለብ ተጫዋቾች በህይወት ያለፈው ታምሩን የሚዘክር ባነር አሰርተው ወደ ሜዳ ይዘው በመግባት የመታሰቢያ ፎቶ ሲነሱ ተመልክተናል።

በተመሳሳይ ምንም እንኳን በፕሪሚየር ሊጉ በሚገኙ ክለቦች ተጫውቶ ባያሳልፍም ሀዘኑ በእግርኳሱ ከባቢ ውስጥ በመሆኑ ፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቹን በይፋ ለመዘከር ይህ ነው የሚባል ጥረት አለማረጉ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር።

👉ከቆሙ ኳሶች መነሻ ያደረጉ ግቦች

በጨዋታ ሳምንቱ በነበሩ ስምንት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ከቆሙ ኳሶች(ቅጣት ምት እና የማዕዘን ምት) ተቆጥረዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ሀቢብ ከማል እና የመከላከያው ግሩም ሀጎስ በቀጥታ አስገራሚ የቅጣት ምት ግቦችን ማስቆጠር ሲችሉ የተቀሩት ደግሞ ከመዕዘን ምት እና ከቅጣት ምት ከተሻሙ ኳሶች ተቆጥረዋል።

ግቦቹ የተቆጠሩበት መንገድ በአጋጣሚ ወይንስ በልምምድ ሜዳ ክለቦች በትኩረት ሰርተው የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የምንመለከተው ቢሆንም በዚህ መጠን ግቦች የመቆጠራቸው ጉዳይ ግን ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ ነበር።

👉የስንታየሁ መንግስቱ መለያ

በወላይታ ድቻ ቤት ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ሆነ ዘንድሮ የቡድኑ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ስንታየሁ መንግሥቱ ከጉዳት ጋር እየተጋለ ቢሆንም ለቡድኑ የተቻለውን ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ታድያ ከዚህ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የሚጠቀመው መለያ ጉዳይ ነው። ወላይታ ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በወጥነት እየተጠቀማቸው በሚገኙት በአረንጓዴ እና ነጭ አማራጮች በቀረቡት የክለቡ መለያዎች ላይ መጠነኛ የይዘት ማሻሻያ በማድረግ እየተጠቀመ ይገኛል።

የክለብ ይፋዊ መለያ አንገቱ ክብ (Round Neck) ሲሆን ስንታየሁ ግን በውል በማይታወቅ ምክንያት አንገቱ አካባቢ መጠነኛ ማሻሻያዎችን አስደርጎ ቪ ቅርፅ(V Neck) እንዲሆን አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል።

ምናልባት ክለቡ በጥቅሉ ከመጫወቻ መለያ ጋር ተያይዞ ችግሮች ያሉበት ሲሆን በተመሳሳይ የአዲስ ህንፃ እና የአንተነህ ጉግሳ መለያ አንገቱ አካባቢ የተቀደደ ስለመሆኑ ማስተዋል ችለናል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ ምናልባት የክለቡ መለያ የቆየ ከመሆኑ የተነሳ በመለያው በስተጀርባ የቀደሙ ተጫዋቾች ስም በጥለት ተሸፍኖ እየተመለከትን እንደመገኘታችን የክለቡ ሰዎች ይህን ጉዳይ በአንክሮ ሊመለከቱት ይገባል።