የ “Football for school” ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከፊፋ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው Football for School የአሰልጣኞች ስልጠና መርሐ ግብር ይፋዊ የመክፈቻ ፕሮግራም ዛሬ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተከናውኗል።

ይህ የፊፋ ፕሮጀክት ከአምስት ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ 100 ህጻናት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ 60 ትምህርት ቤቶች በተወጣጡ  መምህራን አማካኝነት የስልጠና መርሐግብሩ የተጀመረ ሲሆን ጥሪ ከተደረገላቸው 60 መምህራን ውስጥ 54ቱ ተገኝተው የአሰልጣኝነት ስልጠናን መውሰድ ጀምረዋል።

ዛሬ በተደረገው ይፋዊ የመክፈቻ መርሐግብር የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋትማ ሳሙራ ፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ አቶ የሰውዘር በላይነህ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተካሄደው ፕሮግራም ላይ በቅድሚያ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ይህንን መርሐግብር በማስጀመራቸው የተሰማቸውን ክብር ገልጸው ፊፋ እግርኳስ ጊዜ የሚያባክን እና ከትምህርት የሚያዘናጋ ነገር ነው የሚለውን በመስበር ይህንን ፕሮግራም በማዘጋጀቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም ለፊፋዋ ዋና ፀሐፊ ፋትማ ሳሙራ እግርኳሱን የተሰጥኦ መጀመሪያ ወደ ሆኑት ትምህርት ቤቶች በማምጣታቸው አመስግነው ለአሰልጣኝ መምህራን ጠንክረው እንዲሠሩ እና የልጆቹ ስኬትም ሆነ ውድቀት በነሱ የተወሰነ እንደሆነ ጠቁመው በመጨረሻም የፊፋ ዋና ፀሐፊነታቸውን  በያዝነው ዓመት ለሚያጠናቅቁት ፋትማ ሳሙራ በቀሪ ሕይወታቸው በጎ ነገር እንዲያጋጥማቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የትምህርት ሚኒስትር ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ በከፍተኛ አፈጻጸም መሬት የወረደ ሥራ መሥራታቸውን እና ኢትዮጵያ ይህንን ፕሮግራም በመጀመር ከምስራቅ አፍሪካ ሦስተኛ ሀገር መሆኗ እንዳኮራቸው ስሜታቸውን በማጋራት ንግግራቸውን አገባደዋል።

በመቀጠል ከትምህርት ሚኒስትር ተወክለው ንግግር ያደረጉት አቶ የሰውዘር በላይነህ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 456 ሺህ ትምህርት ቤቶች 37,800 የሚሆኑት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ በመጠቆም ዛሬ ለተከፈተው ፕሮግራም የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ለፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋትማ ሳሙራ የእንኳን ደኅና መጣሽ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ በትምህርት ቤት ዙሪያ ስለምትሠራው ነገር ምስጋና አቅርበዉላታል። አምባሳደሩ አክለውም እንደ ሀገር በምንፈልገው ደረጃ በእግር ኳሱ ዕድገት አለማስመዝገባችንን አውስተው ይህ ፕሮግራም ግን ለአፍሪካ ወርቃማ ዕድል እንደሆነ እና ፊፋም ይህን ዕድል ለኢትዮጵያ በማመቻቸቱ የተሰማቸውን አድናቆታት እና ምስጋናቸውን አቅርበው ፕሮግራሙን ለማጠናከር እና ውጤታማ ለማድረግ ተቋማቸው ከትምህርት ሚኒስትር እና ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ እና የኢትዮጵያ እግርኳስም እንደሚያድግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በመጨረሻ ንግግር ያደረጉት የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋትማ ሳሙራ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ 48 ሀገራት የሚሳተፉ በመሆኑ ከአፍሪካ 9 ሀገራት እንደሚቀላቀሉ ጠቁመው ኢትዮጵያም ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ማጣሪያውን እንድታልፍ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው ዛሬ የተጀመረው የ Football for school ፕሮግራም ዋና ዓላማ ለህጻናቱ የሕይወት ክህሎት ስልጠና መስጠት እንደሆነ ጠቁመው የፊፋ አባላት ከሆኑ 211 ሀገራት ውስጥ 102 የሚሆኑ ሀገራት ውስጥ ይህ ፕሮግራም እንደተጀመረ ገልጸዋል። በመጨረሻም ፕሬዝዳንቷ ለ2023ቱ የኒውዚላንድ እና አውስትራሊያ የሴቶች ዓለም ዋንጫ ያገለገለች ኳስ ላይ ፊርማቸውን አኑረው ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ከሰጡ በኋላ ይፋዊ የመክፈቻ መርሐግብር ተካሂዶ የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል።