የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ ቅሬታ አቅርቧል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት ጨዋታውን ሲያደርግ በነበረው የዓየር ሁኔታ እና በቀጣይ የጨዋታ ሰዓት ዙሪያ ፌዴሬሽኑ ለፊፋ ደብዳቤ ልኳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሴራሊዮን ጋር ተጫውቶ ያለ ጎል አቻ መለያየቱ ይታወሳል። ጨዋታው በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ለዕይታ አስቸጋሪ በመሆኑ ሁለተኛው አጋማሽ መጀመር ከነበረበት 30 ደቂቃዎች ያህል ዘግይቶ ሲጀመር በሁለተኛው አጋማሽ ለተጨማሪ ሁለት ጊዜያት (78ኛው እና 89ኛው ደቂቃ ላይ) ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።

ይህንን ጠቅሶ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ለፊፋ ያሳወቀ ሲሆን በዚህ የአየር ሁኔታ ጨዋታ ሊቀጥል መደረጉ አግባብ አለመሆኑን እና ለቀጣይ ጊዜ መተላለፍ ቢኖርበትም አለመደረጉ ፍትሐዊ እንዳልሆነ በደብዳቤ ቅሬታውን ገልጿል።

በተያያዘ መረጃ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀጣይ ኢትዮጵያ ከቡርኪና ፋሶ የምታደርገው ጨዋታ ሰዓት ላይ ለውጥ እንዲደረግ ለፊፋ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን እየተመለከተ እንደሆነ እና በፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጥ ፊፋ አሳውቋል ሲል ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አሳውቋል።