ከፍተኛ ሊግ | የ2ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ይርጋ ጨፌ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ቤንች ማጂ ቡና ፣ ሸገር ከተማ እና ቢሾፍቱ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

የ3:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ስልጤ ወራቤ እና ይርጋጨፌ ቡናን ሲያገናኝ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ አጨዋወት የተመለከትንበት አጋማሽ ሆኖ አልፏል። በአጋማሹ ስልጤ ወራቤ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የበላይነቱን በመውሰድ በተደራጀ የኳስ ቅብብል የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ይርጋጨፌ ቡና በአንጻሩ ኳስን ለተጋጣሚው ቡድን በመተው መከላከልን ምርጫው አድርጎ የሚያገኙትን ኳሶች በተደራጀ መልኩ ክፍተቶችን ለመጠቀም በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ሲፈጥር ተስተውሏል። በ8ኛው ደቂቃ ይርጋጨፌ ቡና ከጥልቀት የተገኘውን ኳስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በመሄድ ከአቤኔዘር ከፍያለው የተሻገረለትን ኳስ ዘላለም አበራ ወደ ግብ ቀይሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤ በተመሳሳይ አጨዋወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጎ ግብ ማስቆጠር ሰይችል አጋማሹ ተጠናቋል።

በስልጤ ወራቤ በኩል የተጫዋች ቅያሪ ተደርጎ የኃይል ሚዛኑ ወደ ስልጤ እስከሚያመዝን ድረስ ጥሩ እና ተመጣጣኝ ጨዋታን ያሳየን የሁለተኛው አጋማሽ ተመልክተናል። ሆኖም በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራ ተሽሎ የተገኘው ስልጤ ወራቤ የይርጋጨፌን የግብ ክልል ለመድፈር ተቸግረው ውለዋል። በይርጋጨፌ በኩል ከፍተኛ እና በጥንቃቄ የተሞላ የመከላከል ስልት በመከተል ግብ ላለማስተናገድ ጥረት አርጓል። ሆኖም በ85ኛው ደቂቃ ስልጤ ወራቤ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ተቀይሮ በገባው የይርጋጨፌ ቡናው ያብስራ ተሾመ ከግብ ውስጥ አውጥቶታል። ጨዋታውም በዚሁ ቀጥሎ በ90+3ኛው ደቂቃ ላይ የይርጋጨፌው ተቀይሮ የገባው አማኑኤል በቀለ በፈጣን ሽግግር ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሯል። ጨዋታውም በይርጋጨፌ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ለ የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ በሆነው የአርባምንጭ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ጨዋታ በአዞዎቹ የበላይነት ተጠናቋል። ከጨዋታው ጅምር አንስቶ በሜዳ ላይ የተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት አርባምንጮች 8ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። ከግቡ ትይዩ የተገኘን የቅጣት ምት አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን አክርሮ በመምታት ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። የጨዋታውን የሐይል ሚዛን በይበልጥ ወደ ራሳቸው በማድረግ መጫወትን የቀጠሉት አርባምንጮች 26ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ልክ የመጀመሪያዋ ጎል ከተቆጠረችበት ቦታ ላይ የተገኘችን የቅጣት ምት የግራ ተከላካዩ ሠለሞን ሀብቴ በድንቅ ምት ወደ ግብነት ለውጧታል። ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የጣሩት የአሰልጣኝ ደረጀ በላዩ ወሎ ኮምቦልቻ ከዕረፍት በፊት በማኑሄ ጌታቸው አማካኝነት ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን ግብ አስቆጥረዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ ተመልሶ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አርባምንጮች ዳግም የጨዋታ ብልጫን ወስደው መጫወትን ቀጥለው 71ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ፍቅር ጌታቸው ሦስተኛ ግባቸውን አግኝተው ጨዋታው በመጨረሻም 3ለ1 በሆነ የአርባምንጭ ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።

የ05:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሞጆ ከተማ እና ቤንች ማጂ ቡናን ሲያገናኝ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ ታይቷል።  በአጋማሹ ቤንች ማጂ ቡና በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የበላይነቱን በመውሰድ እና በአጭር የኳስ ቅብብል የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ሞጆ ከተማ በአንጻሩ ኳመከላከልን ምርጫው አድርጎ የሚያገኙትን ኳሶች በረጃጅም ቅብብል ክፍተቶችን ለመጠቀም በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ሲፈጥር ተስተውሏል። በ30ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡና የተገኘውን ኳስ በፈጣን ቅብብል የተገኘውን ኳስ ሀሰን ሁሴን ወደ ግብ ቀይሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሞጆ ከተማ በተሻለ መልኩ ተጫውተው የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ጨዋታ እና ጥሩ ጥሩ የግብ እድል ተመልክተናል። ሞጆ ከተማ ከመጀመሪያው አጋማሽ ስህተታቸው ታርመው የተሻለ ተጫውተዋል ። ይህንንም ተከትሎ በ52ኛው ደቂቃ ሞጆ ከተማ ያገኘውን የግብ እድል በብሩክ ግርማ አማካኝነት አስቆጥሯል። ጨዋታው በዚው ሁኔታ ቀጥሎ በ66ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ያገኘውን ቅጣት ምት ወንድማገኝ ኪራ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሞጆ ከተማዎች ፈጣን እና ሀይል የቀላቀለ ጨዋታ አስመልክተውናል። ቤንች ማጂ ቡና የጨዋታውን ፍጥነት በማቀዝቀዝ እና የሚያገኙትን የግብ እድል ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት አርገዋል። ተሳክቶላቸውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርባቸው 2-1 መርታት ችለዋል።

ሀዋሳ ላይ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሸገር ከተማ እና ካፋ ቡና መካከል የተካሄደ ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ሀያ ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ አቀራረቦችን ማስተዋል ብንችልም የኋላ ኋላ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መያዝ የቻሉት ሸገሮች 36ኛው ደቂቃ ላይ በአላዛር ሽመልስ አማካኝነት የመሪነት ጎላቸውን አግኝተዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የካፋ ቡና የግብ ክልል የተሻማን የቅጣት ምት ምንተስኖት መንግሥቱ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የቡድኑን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። አጋማሹ ሊገባደድ የማሳረጊያ በሆነው 45ኛ ደቂቃ አካባቢ ከባህርዳር ሸገር ከተማን የተቀላቀለው ፋሲል ፋሲል አስማማው ተጨማሪ ጎል ከመረብ አሳርፏል። ከዕረፍት መልስ 47ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ሽመልስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛዋን ጎል በማከል ጨዋታው በሸገር ከተማ የ4ለ0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

የ08:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ወልዲያ እና ንብ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን የማጥቃት ሸግግር ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ባልተረጋጋ እንቅስቃሴ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዋል። መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ወልዲያዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ወንድማገኝ ሌራ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በኃይሉ ተስፋየ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ሆኖም ግን ንቦች 44ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አብርሃም አሰፋ ከነካው በኋላ ያገኘው ናትናኤል ሰለሞን በግሩም ክህሎት ታግዞ አስቆጥሮታል።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት ጨምሮ ሲቀጥል ተሻሽለው የቀረቡት ንቦች 57ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ የተሰጠውን የቅጣት ምት ናትናኤል ሰለሞን በአስደናቂ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎት ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። በአስር ደቂቃዎች ልዩነትም ተቀይሮ የገባው ኤርሚያስ ደረጄ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ወልዲያዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በድሩ ኑርሁሴን አስቆጥሮት ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

ከቀትር በኋላ በምድብ ‘ለ’ ሦስተኛው መርሀግብር ጨዋታው ሲቀጥል አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን ከ ጋሞ ጨንቻ አፋልሟል። በመጀመሪያው አጋማሽ 16ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ተስፋዬ አዲስ ከተማን መሪ ቢያደርግም ጨዋታው ሊቋጭ አንድ ደቂቃ ሲቀረው 89ኛ ደቂቃ ሠለሞን ብሩ በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ 1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ፍፃሜን አግኝቷል።

የ10:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ላይ በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ሲገናኙ መጠነኛ ፉክክር የታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጉሽሚያዎች የበዙበት እና ብዙ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። 35ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስወጣት የሞከረው የኮልፌው ሳሙኤል ወንድሙ የገጨው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ ራሱ መረብ ላይ ሊያርፍ ለጥቂት በአግዳሚው በኩል ወጥቷል። ያንኑ ኳስ በቀኝ መስመር ከተገኘው የማዕዘን ምት ሲሻማ ያገኘው ተመስገን አማረም በግንባሩ በመግጨት ያልተጠበቀ ግብ አድርጎታል። ሆኖም ግን አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ኮልፌዎች የአቻነት ግብ አስቆጥሮታል። ሉካ ፓውሎ ረጅም ርቀት ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ የግብ ጠባቂው ትኩረት ማጣት ተጨምሮበት መረቡ ላይ አርፏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ኮልፌዎች በቀሪዎቹ 20 ደቂቃዎች ደግሞ ጅማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባልነበረበት አጋማሽ በጅማ አባ ጅፋሮች በኩል 66ኛው ደቂቃ ላይ ገለታ ኃይሉ ከግራ መስመር ያሻማው እና አቡበከር ገጭቶት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት 79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ጌትነት ታፈሰ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ሳይዘጋጅ ያገኘው ፊልሞን ገብረጻድቅ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት የወጣው ኳስ በኮልፌዎች በኩል ደግሞ 87ኛው ደቂቃ ላይ ቃለጌታ ምትኩ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ መትቶት ግብ ጠባቂው የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ሀዋሳ ላይ የዕለቱ የማሳረጊያ በሆነው ጨዋታ ቢሾፍቱ ከተማ በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ጎሎች የመዲናይቱን ተወካይ የካ ክፍለ ከተማን 2ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል። የቀድሞው የሀዋሳ እና ወላይታ ድቻ አማካይ ነጋሽ ታደሠ እና ዳዊት ሽፈራው የቢሾፍቱን የድል ግቦች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።