ከፍተኛ ሊግ | የ2ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ በተከወኑ ስድስት ጨዋታዎች ሲቋጭ በምድብ ‘ሀ’ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀላባ ከተማ በምድብ ‘ለ’ ደግሞ ነጌሌ አሪሲ እና ደሴ ከተማ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

የ03:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ላይ የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ሲያገናኝ ገና በ1ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ያገኘውን ግልፅ የግብ ዕድል ቢቂላ ሲሪታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታው አዲስ አበባ ከተማ ኳስን በመቆጣጠር ረጅም እና አጫጭር ኳስን በመጠቀም የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። በአንፃሩ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ኃይልን የቀላቀለ እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አሳይቷል።  በ26ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ከርቀት የተገኘውን ኳስ አብዱለሂ አሊዩ አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሯል። አዲስ አበባ ከተማ አፀፋውን ብዙም ሳይቆይ በ28ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ኤርሚያስ ኃይሉ አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ብዙ ኃይል የተቀላቀለ አጨዋወት እና ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር ተመልክተናል። በጥንቃቄ የታጀበው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል በ89ኛው ደቂቃ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የጫዋች የሆነው አብዱላሂ አሊዩ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በ1-1 ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በምድብ ‘ለ’ ሀዋሳ ላይ ደብረብርሃን ከተማን ከነገሌ አርሲ ያገናኘው መርሀግብር የሁለተኛ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴን መመልከት ባንችልም ከደቂቃ ደቂቃ ወደ ጨዋታው ሲገፋ በተሻለ ግለት ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ነጌሌ አርሲዎች በድግግሞሽ የደብረብርሃን የሜዳ ክፍል ላይ በመድረስ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲታትሩ አስተውለናል። በአንፃሩ ኳስን በመያዝ መሐል ሜዳ ላይ ረጅሙን ደቂቃ ሲያሳልፉ የተመለከትናቸውን ደብረብርሃን ከተማዎች በበኩላቸው በማጥቃቱ ረገዴ የነበራቸው ጥረት እምብዛም ሆኖ መመልከት ችለናል።

ከዕረፍት መልስ ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ለመጫወት ሲጥሩ የተስተዋሉት የአሰልጣኝ በሽር አብደላው ነገሌ አርሲ 56ኛው ደቂቃ ላይ ጎል የማሸነፊያ ጎላቸውን ወደ ካዝናቸው ከተዋል። ግብ ጠባቂው ወርቅነህ ዲባባ ለማቀበል የፈጠረው ስህተት ተጠቅሞ ምንተስኖት ተስፋዬ ከሳጥኑ ጫፍ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፏታል። ጨዋታውም በነገሌ አርሲ 1-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

የ08:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ነቀምቴ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ኤሌክትሪኮች የተሻሉ ነበሩ። 24ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ የግብ ዕድል በነቀምቶች ሲፈጠር አብዲ ተሾመ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታው 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ኤሌክትሪኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሚካኤል ሀሊሲ እንዳለ ዘውገ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቢኒያም ካሳሁን አስቆጥሮታል። ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥም እሱባለው ሙሉጌታ ከግራ መስመር ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ያሬድ የማነ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎት የኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪነት አጠናክሯል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመግባት የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች 50ኛው ደቂቃ ላይ በመሳይ ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ 57ኛው ደቂቃ ላይም በእሱባለው ሙሉጌታ አማካኝነት ሦስተኛ ግብ አስቆጥረዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ተቀዛቅዘው የቀረቡት ነቀምቴዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ የምድብ ‘ለ’ ፍልሚያ ከሰዓትም ቀጥሎ ኦሜድላን ከደሴ ከተማ አገናኝቷል። በሁለቱ መስመሮች በኩል በሚነሱ አልያም ከመሐል ክፍሉ በሚጣሉ ኳሶች የማጥቃት አማራጭን የተከተሉት ደሴ ከተማዎች በፈጠሩት ጫና 29ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግብተዋል። የኦሜድላ ተከላካዮች ከራሳቸው ሜዳ ኳስን በአግባቡ ማፅዳት አለመቻላቸውን ተንተርሶ እግሩ ስር የገባችውን ኳስ ታፈሰ ሠርካ መረቡ ላይ አስቀምጧት የዳዊት ታደለውን ደሴ መሪ አድርጓል። በይበልጥ ለኋላ ክፍላቸውን ሽፋን በመስጠት የተጠመዱት እና በይበልጥ በመልሶ ማጥቃት ሊጫወቱ የሚሞክሩት ኦሜድላዎች ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ደካሞች በመሆናቸው የጠሩ ዕድሎችን ወደ ጎልነት ለመለወጥ አልታደሉም።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽም ተመልሶ ቀጥሏል። ኦሜድላዎች ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት የተጫዋች ቅያሪን ካደረጉ በኋላ በይበልጥ የተሻለ አቀራረብን ሲያሳዩን ተመልክተናል። ለዚህም ማሳያው ማሙሽ ዳባሮ ተቀይሮ በመግባት ጎል ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ኳሷ በረዳት ዳኛው ተሽራለች። ጎሏ መሸሯን ተከትሎ የኦሜድላ ተጫዋቾች ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ የነበረ ሲሆን በረዳት ዳኛውም ላይ ቡድኑ ክስን ካስያዘ በኋላ ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሏል። ኦሜድላዎች ወደ አቻነት ለመሸጋገር በተደጋጋሚ በሰይፋ ዛኪር አማካኝነት ግልፅ አጋጣሚዎችን ማግኘት ቢችሉም የተገኙትን ወደ ጎልነት መለወጥ ባለ መቻላቸው 87ኛው ደቂቃ ላይ ደሴዎች ሁለተኛ ጎልን አስቆጥረውባቸዋል።

ጉልላት ተሾመ ከመሐል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ አበሽ ደርቤ በአግባቡ በመቆጣጠር ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት በጥሩ አጨራረስ ጎል አድርጓል። ጎሏ በምትቆጠርበት ወቅት የኦሜድላው ተከላካይ ተመስገን ታሪኩ ረዳት ዳኛውን ለመደብደብ በመጋበዙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ጨዋታውም በደሴ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል።

የ10:00 ጨዋታዎች

በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በጅማ አባ ቡና እና በሀላባ ከተማ መካከል ሲደረግ የሣምንቱ ምርጥ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ሀላባዎች ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ጅማዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይም ጅማ አባ ቡናዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ጥላሁን ቦቶ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ የሀላባው ተከላካይ አሳልፍ መኮንን በግንባሩ ገጭቶ ለማውጣት ሲሞክር ኳሱ የራሱ መረብ ላይ አርፏል። በስድስት ደቂቃዎች ልዩነትም ዘላለም አበበ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ እስካሁን ከተቆጠሩት ግቦች መካከል የውድድሩ ድንቅ ግብ ሆኖ መረቡ ላይ አርፏል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ሀላባዎች በአጋማሹ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን 20ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ፀጋ ከድር በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገው ግሩም ሙከራ በግብ ጠባቂው እና በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ጅማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው እስጢፋኖስ ተማም በቀነሰለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ያሬድ መሐመድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሀላባዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከማዕዘን በተሻማ ኳስ ያደረጉት ሙከራ በግቡ አግዳሚ ሲመለስባቸው 83ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ አስቆጥረዋል። ሰለሞን ያለው አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ወሰን ጌታቸው በግሩም አጨራረስ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በመምታት ግብ አድርጎታል። በተደጋጋሚ ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገው ወሰን ጌታቸው ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ግብ ሲያስቆጥር በርበሬዎቹ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ አራተኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ የሆኑበትን ግብ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አግኝተዋል። ሰለሞን ያለው ድንቅ በሆነ ዕይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ የተቆጣጠረው ፀጋ ከድር አስደናቂ በሆነ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎት ሀላባ ከተማ በሁለት ግብ ከመመራት ተነስቶ የ 3-2 ጣፋጭ ድል እንዲጎናጸፍ አስችሏል።

የምድብ ‘ለ’ የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ቦዲቲ ከተማ እና ባቱ ከተማን አገናኝቶ ተቋጭቷል። ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር እና ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴን ያየንበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ቤቱ በመልሶ ማጥቃት ደግሞ ቦዲቲ አቀራረባቸው አድርገው ሲጫወቱ ታይቷል። ፈጠን ባለ የመስመር የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ ከጅምሩ መከተል የጀመሩት ቦዲቲዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረው ቀዳሚ ሆነዋል። ከግራ የባቱ የግብ ክልል ወደ ውስጥን የተሻማን ኳስ አምበሉ ተመስገን ሽብሩ ለማውጣት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ማሞ አየለ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯታል። ምላሽ ለመስጠት በአንድ ሁለት አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የሚደርሱት ባቱዎች በወንድማገኝ እያሱ አማካኝነት ካደረጉት ግሩም ሙከራ በኋላ የአቻነት ጎልን አስቆጥረዋል። 20ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ወንድወሰን በለጠ ያመቻቸለትን ኳስ ዮናታን አምባዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።

ከዕረፍት መልስ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መቀጠል ቢችልም ከመጀመሪያው አጋማሽ አኳያ በብዙ ረገድ ወርዶ በእንቅስቃሴም ይሁን የጠሩ የግብ ዕድሎችን መመልከት ሳንችል 1ለ1 በመጨረሻም ጨዋታው ተቋጭቷል።