ሪፖርት | ሉሲዎቹ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሊን ረተዋል

በ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ማሊን 4-0 መርታት ችላለች።

የኢትዮጵያ እና የማሊ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የ3ኛ ዙር የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲደረግ ቀን 9 ሰዓት ላይ በቤኒኗ ዋና ዳኛ ዞንግቦሲ ጎቾኤዱ ፊሽካ አማካኝነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ ፉክክር ተደርጎበታል ሆኖም ግን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ ነበር።

በሚያገኙት ኳስ አልፎ አልፎ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሚያደርጉት ሉሲዎቹ 15ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ሙከራቸውን አድርገዋል። መዓድን ሳህሉ ንግሥት በቀለ እና እሙሽ ዳንኤል ተቀባብለው ባመቻቹላት ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባታል።

የማሊ ተጫዋቾችን ክፍት ቦታ በማሳጣት እና በተሻለ የራስ መተማመን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘችው እሙሽ ዳንኤል በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። አጥቂዋ በአሥር ደቂቃዎች ልዩነትም ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በኢትዮጵያ 2-0 መሪነት ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችላለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ሉሲዎቹ በማራኪ እንቅስቃሴ ሙሉ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይም መሃል ሜዳው ላይ ግሩም እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው መዓድን ሳህሉ  እየገፋች የወሰደችውን ኳስ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥኑ ጠርዝ መሬት ለመሬት በመምታት ግብ አድርጋዋለች። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም መሣይ ተመስገን መዓድን ካስቆጠረችበት በተቃራኒው የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ የኢትዮጵያ መሪነት ወደ አራት ግብ ልዩነት ከፍ ማድረግ ችላለች።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ በኩል ተቀይራ የገባችው ማሕሌት ምትኩ ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ ስትችል የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆኑት ማሊዎች በሙሉ ደቂቃ አንድም የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው በኢትዮጵያ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በድምር 6-0 የሆነ ውጤት ያስመዘገቡት ሉሲዎቹ በመጨረሻው ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ይህንን ጨዋታ በደርሶ መልስ የሚያሸንፉ ከሆነም በ 2024 በኮሎምቢያ አዘጋጅነት ለሚደረገው ከ 20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል።

*የዛሬውን ድል ምክንያት በማድረግም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ለሁሉም የቡድኑ አባላት የ10 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል።