አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

“ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ እንድትፅፍ ከሙያየ በፊት ምኞቴ ነው”

“ለቀጣዩ ጨዋታም ተገቢውን ዝግጅት በትኩረት እናደርጋለን”

“በብዙ ቁጭት ተነስተን ከዓምናው ቡድን የተሻለ ርቀት እንደምንሄድ ተስፋ አደርጋለሁ”

“ፌዴሬሽኑ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ቢያዘጋጅልን መልካም ነው”

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ መጨረሻው ዙር ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው…

“የዛሬውን ጨዋታ ብዙ ትኩረት አድርገንበት ነው የመጣነው። ከሜዳ ውጪ አሸንፈን ብንመጣም በሜዳችን ጥሩ መሥራት እንዳለብን ተነጋግረን ከተጫዋቾቻችን ጋር ብዙ ሥራዎችን ስንሠራ ነበር። ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ብዬ አስባለሁ።”

ከሌላው የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ የነበሩ ተጫዋቾችን ለረጅም ደቂቃዎች ስለተጠቀሙበት ምክንያት….

“ተጫዋቾቹን ብዙ ሰዓት መጠቀሙ ይሄ የአሰልጣኞች ሥራ ነው የሚሆነው ፤ የእኔ ሥራ ስለሆነ እኔ ወስኜበታለሁ።”

ስለ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ሞሮኮ…

“ሞሮኮ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። የሞሮኮን ጠንካራ እና ደካማ ጎንም ለማወቅ እንደ ሀገር ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል። ከዚ በፊት እንደምንዘጋጀው ለቀጣዩ ጨዋታም ተገቢውን ዝግጅት በትኩረት እናደርጋለን።”

ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ስለማግኘታቸው እና
ባለፉት ዓመታት መጨረሻው ዙር ላይ ውጤታማ ስለማንሆንበት ምክንያት እና ስለሚደረገው ማስተካከያ…?

“የማሊን ቡድን እዚህ እንደጠበቅነው አልነበረም። እዛ ስንገጥመው ሜዳቸው ላይ ብዙ ፈትነውናል በመጀመሪያው አጋማሽም ግብ አላስቆጠርንም ነበር ዛሬ ግን ሁለት አግብተናል ይሄም አንዱ ማሳያ ነው። እነሱ መርጠው የመጡት ጥቅጥቅ ብለው መጫወትን ነው የመጀመሪያዎቹን 35 ደቂቃዎች ተቸግረን ነበር። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ባንጠቀምም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ እንቸገር ነበር እዛ እንደውም የተሻለ ወደ ግብ እንደርስ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻሉ ተጫዋቾችን አስገብተን የማሊን አቀራረብ ለማፈራረስ ጥረት አድርገናል። ከስህተታችሁ ተምራችኋል ወይ ለሚለው ይህ ቡድን ከዓምናው ከ20 ዓመት በታች ቡድን እና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ድብልቅ ነው። ከዓምናው ከ20 አመት በታች ቡድን በዚኛው ቡድን ውስጥ ያለው 5 ተጫዋቾች ብቻ ናቸው። ከአምናው ከ17 አመት በታች ቡድን ደግሞ 13 ተጫዋቾች አካተናል። ዘንድሮ በብዙ ቁጭት ተነስተን ከዓምናው ቡድን የተሻለ ርቀት እንደምንሄድ ተስፋ አረጋለሁ።”

የቀጣዩ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳ ውጪ መሆኑ…?

“የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ማድረጋችን ጥሩ ጥቅም አለው ብዬ አስባለሁ ያ ማለት ግን ሥራ ካልሠራንም ጥቅም ይኖረዋል ማለት አይደለም። የአሁኑ የተሻለው የሴቶቹ ውድድር አሁን ይጀመራል። ተጫዋቾችን ከዛ ውድድር ላይ መጥራት ጥሩ ጥቅም ይኖረዋል ፤ ስቸገርበት የነበረው ትልቁ ነገር እሱ ስለነበር ማለት ነው። የመጀመሪያውን ጨዋታ ሞሮኮ ላይ ሄደን ማድረጋችን ብዙ ነገሮችን ይቀርፋል ብዬ አስባለሁ። ሞሮኮ በጣም ሚሠራበት ብሔራዊ ቡድን ስለሆነ በምን መንገድ መቅረብ አለብን ለሚለው ትናንት ከትናንት ወዲያ ከነበረኝ ተሞክሮ ተነስቼ የተሻሉ ነገሮችን ለመሥራት ገና ከአሁኑ ሥራዬን መጀመር እንዳለብኝ አምናለሁ። ፌዴሬሽኑም በነዚህ ክፍት ጊዜያት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ቢያዘጋጅልን መልካም ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ እንድትፅፍ ከሙያየ በፊት ምኞቴ ነው። ሚዲያዎችም ተጫዋቾችን በጥሩ መንገድ ብታነሳሱ ጥሩ ነው እላለሁ።”