ዛሬ ሊቢያ ላይ የሚደረገው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮጵያዊያን ዳኞች ይመራል

የሱዳን እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እንደሚመሩት ታውቋል።

በአፍሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በምድብ ሁለት ተደልድለው እያደረጉ የሚገኙት ከቶጎ ጋር 1ለ1 የሆነ ውጤት ያስመዘገበችው ሱዳን እና ሞሪታኒያ ላይ የ2ለ0 ድል የተቀዳጀችው  ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ዛሬ ምሽት  1 ሰዓት ላይ በሊቢያው ማርታየርስ ኦፍ ቤኒያ ስታዲየም እርስ በእርስ በመጫወት የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያከናወናሉ።

ይህንን ጨዋታም ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ዳኞች እንደሚመሩት የታወቀ ሲሆን በዚህም በአምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት ፣ ተመስገን ሳሙኤል እና ፋሲካ የኋላሸት በረዳትነት ፣ ዛሬ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚመራው ለሚ ንጉሤ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ለመምራት ስለመመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ አመላክቷል።