​የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ከተማን ካሸነፈ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።


አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ውጤት ስለማጣታቸው 

“አብዛኛው ተጫዋች ማጥቃትም ላይ ያሉት ከተወሰኑት በስተቀር ልምድ ይጎላቸዋል። በጋራ ከመጫወት ይልቅ በግል የመጫወቱ ነገር ስላለ ይሄ ነገር በእጅጉ ጎድቶናል። ምክንያቱ ይሄ ነው። 

ስለበድኑ የሥነልቦና ችግር

“በእርግጥ ይህንን ነገር ለመቅረፍ እንሰራለን ፤ የሥነ ልቦና ባለሙያ የለንም። ግን ለሥነ ልቦና የሚያስፈልገውን ነገር በተቻለን መጠን ለማድረስ እንሞክራለን። ቴክኒክ ዳይሪክተርም አለን ፤ በመተጋገዝ ያንን ነገር ለማቅረፍ እንሰራለን። ግን አሁን ትልቅ እየጎዳን ያለው በፊት የእኛ ቡድን የሚታወቀው በጋራ በመጫወት እና በጋራ ውጤት በማስመዝገብ ነው ። አሁን ግን ይሄን ነገር ትንሽ እያጣነው ስለመጣን ሀሉም በየግል ነው የሚጫወተው።  ይህ የለምድ ጉዳይ ነው። ትንሽ እሱ እየጎዳን ነው የመጣው። 

በቡድኑ ስላላቸው ዕምነት

” እርግጥ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል። በሁለተኛው ዙር አንዳንድ መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች እያስተካከልን ስኳዱም ክፍተት ያለው ስለሆነ የሚሟላ ከሆነ ገና ረጅም ጉዞም አለን። ስለዚህ ያንን ቀርፈን እንመጣለን ብዬ ዕምነት አለኝ።”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ድሉ ስለሚሰጠው ስሜት

“ማሸነፋችን ጥሩ ነው። የመጨረሻውን ጨዋታ ካሸነፍን በኋላ በተከታታይ ሁለት ሽንፈት እና አንድ አቻ ነበር። ስለዚህ ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ነው። ግን ያ ብቻውን አስተማማኝ አይሆንም። አብረን ዘጠና ደቂቃ ካለው እንቅስቃሴ ጋር ማየት አለብን። ከዕረፍት በፊት ቡድናችን ጥሩ ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን በራሳችን የአካሄድ ስህተት ለእነሱ የፈጠርነው የመጫወቻ ቦታ አለ ፤ በዛም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ተፈጥሮ ነበር። ወደ መጨረሻ ላይ ያንን ለማረም ሞክረናል ፤ ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ። የነበረው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሲታይ መታረም ያለበት ነገር አለ። ከውጤት አንፃር ግን ጥሩ ነው።

ስለውጤቱ አስገላጊነት

“ይሄ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ውጤቱ አስፈላጊ ነው። ግን ጨዋታውን ባልተቆጣጠርንበት ሁኔታ ውጤቱ ምንም ነው። ምክንያቱም ለነገ ዋስትና አይሆንም። አብሮ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲቻል ግን ለነገም አስተማማኝ ነው። ግን ማሸነፋችን ጥሩ ነው።

ስለቡድኑ ተገማችነት

“አንድ የራሱ የሆነ የአጨዋወት ዘይቤ ያለው ቡድን ተገማች ነው። ምንም ነገር ከሌለህ ነው ተገማች የማትሆነው ፤ መገመት ማለት ደግሞ መታወቅ አይደለም። የራስህ ነገር መኖሩ አስተዋፅዖው ያንተን ነገር መነሻ አድርገው ሲመጡ በተዘዋዋሪ ደግሞ እነሱ እንዴት እንደሚመጡ ታውቃለህ ማለት ነው። እነሱ የሚመጡበትን ነገር ማረም ማስተካከል እሱ ተገቢ ነው። ግን ተገማች መሆን ደግሞ አንድ ቡድን አንድ ነገር እንዳለው ነው የሚያሳየው። እነባርሴሎና እነሲቲ እኮ ተገማች ናቸው። ተገማች በሆኑበት ነገር ውስጥ ነው ብልጫውን የሚወስዱት። ስለዚህ ተገማች መሆኑ ይቀጥላል። ምንም ነገር ሳይኖረን ሲቀር ግን ተገማች አንሆንም።”