የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-0 ሀዋሳ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ባህርዳር ከተከታታይ ውጤት ማጣት መልስ ሶስት ነጥብ ከሀዋሳ ካገኘበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ድሉ

“ጥሩ ነበር፡፡ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ማሸነፍ መመለሳችን ተጫዋቾቻችን ላይ የሚፈጥረው ስነ ልቦና ትልቅ ነው ብዬ ነው የማስበው። ከዛ ውጪ ወደ ጨዋታው ስመለስ በመጀመሪያው አርባ አምስት ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ብልጫ ወስደን ብዙ ማግባት የነበረብንን ኳሶች አምክነን ነው የወጣነው። ሁለተኛው አርባ አምስት ግን ያው ቅድም እንዳልኩህ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ለማሸነፍ ስትፈልግ የያዝካትን አንድ ጎል የያዝካትን ነጥብ ማስጠበቅ ነው የምትፈልገው፤ እና ልጆቻችን ወደ ኃላ በመሸሻቸው ሀዋሳዎች ትንሽ ጫና እኛ ላይ ፈጥረው ነበር፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ቡድኔ በምፈልገው መልኩ ሄዷል ማለት አልችልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ውጤቱንም አስጠብቆ ለመውጣት ልጆቹ ያደረጉት ተጋድሎ ትልቅ ነበር እና ወጣቶቼን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ስለ ፉአድ ፈረጃ ጎል

“ፉአድ ገና ወጣት ብዙ መስራት የሚችል ለክለብ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የሚጠቅም ትልቅ ጥሩ ተጫዋቾች ነው፡፡ ተስፋ ያለው ተጫዋች ነው፡፡ ትልቁ አቅሙ አንተ የምትሰጠውን ትዕዛዝ ሳይረሳ መተግበሩ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያው ከልጅነት የተነሳ ከልምድ ማነስ የተነሳ ቢሳሳትም አውቆ የሚያደርጋቸው ነገሮች ስላልሆኑ ወደፊት እየታረሙ ይሄዳሉ፡፡ በተረፈ ያገባሁም ጎል ጥሩ ጎል ነው ደስ የሚል ጎል ነው፡፡ ወደፊት ጎል ላይ ከደረሰ ማግባት እንደሚችል ያሳየዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለ ኦሴ ማውሊ መመለስ

“የህክምና ባለሙያዎች የነገሩን ከዚህ በኋላ እስከ ሦስት ሳምንት እንደሚፈጅበት ነው፡፡ ግን ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ወደ መደበኛው ልምምድ ተመልሷል፡፡ እሱ ያለበትን ሁኔታ እና ሀኪሞቹ የሚሉትን ሁኔታ ተመለክተን እዚህ ድሬዳዋ ላይ ቢያንስ አንድ ጨዋታ ይጫወታል ብዬ አስባለው፡፡

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ውጤታማ ስላላደረጋቸው ምክንያት

“ቅድም ለመግለፅ እንደሞከርኩት ትንሽ ዛሬ ቡድኔ ላይ አቅም ማነስ ይታያል፡፡ ይሄ የሆነው ባለፈው ልጆቹ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለው ስለነበር ከዛ በኋላ የነበረው ክፍተት ጠባብ ስለነበር ብዙ የአቅም ማነስ ይታይ ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ በእንቅስቃሴ ብልጫ ባይወሰድብንም ብዙ ኳሶችን አግኝተናል አልተጠቀምንም፤ ተቃራኒ ቡድን የሚያገኘውን ተጠቅሟል ማለት ይቻላል፡፡ እንዳገኘነው ብንጠቀም ኖሮ ጨዋታው ይቀየር ነበር። በተለይ ከእረፍት በኋላ ለማስተካከል ሞክረናል። በእንቅስቃሴም የተሻለ ነገር ለማድረግ አስበናል። ግን ያው እየተጫወትን ልክ ቡድኑ እየተነሳ ባለበት ወቅት ነው ሁለተኛው ጎል የገባው። ትንሽ ሁለተኛው ጎል መግባቱ እንደምንፈልገው ተጭነን እንዳንጫወት ተቸግረን ነበር፡፡

ተጠባባቂ ላይ ያሉ ረዳት አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ካርድ ስለማየታቸው

“ያው ውስጥ ያለውን ነገር ማውራት አስፈላጊ ባይሆንም መስተካከል ያለባቸው ለምሳሌ ኳሱን ቶሎ ልንጀምር እናስባለን ግን መሀል የነበረው ዳኛ ቶሎ አያስጀምረውም። በዛ የተነሳ ስሜታዊ እንሆን ነበር በተደጋጋሚ ከዛ አንፃር ነው፡፡አንዳንዴ ሚዛናዊነት ካልታየ ሜዳ ላይ እንደዚህ አይነት ነገር ይነሳሉ እና ይሄን ማሳበብ አስፈላጊ አደለም በእኛ በኩል ያለውን ማረም እንችላለን ከማፍጠን አንፃር እንዲፈጥን ስለምንፈልግ ትንሽ ሲዘገይ በዛ የተነሳ ነው ስሜታዊ የሆኑት ማለት ይቻላል፡፡