ወልቂጤ ከተማ አዲስ አሠልጣኝ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወልቂጤ ከተማ አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸውን አግዶ ሳይጠበቅ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ጋር ከሰሞኑ ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረውን አሠልጣኝ ሾሟል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመንን እስከ አስራ ሁለተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ድረስ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ሲመራ የቆየው ወልቂጤ ከተማ በትላንትናው ዕለት በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ0 ከተረታ በኋላ አሰልጣኝ ጳውሎስ ከክለቡ ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሰጡትን አስተያየት ተንተርሳ ሶከር ኢትዮጵያ ትናንት ምሽት ዘገባ ያቀረበች መሆኑ ይታወቃል።

ከሰሞኑ የከፍተኛ ሊጉን ክለብ ሀምበሪቾ ዱራሜን እንደተቀላቀሉ ገልፀን የነበረው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ደግሞ ዛሬ በጠዋት በረራ ወደ ድሬደዋ የተጓዙ ሲሆን ከሰዓታት በፊትም የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች እና አመራሮች በተገኙበት ከክለቡ ጋር ውይይት እና ትውውቅ እንዳደረጉ ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች። ድረ-ገፃችን ከክለቡ ባገኘችው መረጃም አሠልጣኙ የአንድ ዓመት ውል ፈርመዋል። አሠልጣኝ ተመስገንም ነገ ልምምዱን ካሰራ በኋላ በ13ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀድም የሀዋሳ ከተማን ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች በማሰልጠን የተሳኩ ዓመታት ካሳለፈ በኋላ በዋናው የሀዋሳ ቡድንም ጭምር ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ማገልገል የቻለው ተመስገን የኢትዮጵያ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድንም በማሰልጠን በተመሳሳይ በክለብ ደረጃ የሰራውን ስኬት ማሳካት ችሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ደቡብ ፓሊስን 2012 ላይ በከፍተኛ ሊጉ ካሰለጠነ በኋላ በድጋሚ እስከ ያዝነው ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አሰልጣኝ ሆኖም አገልግሏል።

በተያያዘ ዜና አሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እና ረዳቱ እዮብ ማለ የእግድ ደብዳቤ ደርሷቸው የክለቡን ካምፕ በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ ማምራታቸውን የሰማን ሲሆን አሠልጣኞቹም ሪፖርት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተላልፏል።