ለሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አዲስ አሰልጣኝ ተሾመ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጌዴኦ ዲላን ባለፉት ዓመታት ሲያሰለጥን የነበረው እንዳልካቸው ጫካ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ አሰልጣኝ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ላይ ውጤታማ መሆን ከቻሉ አሰልጣኞች መካከል እንዳልካቸው ጫካ ተጠቃሹ ነው፡፡ በትውልድ አካባቢ ዲላ እና እንዲሁም በተደጋጋሚ በደቡብ ክልል ረጅም ዓመታት የሴት ቡድኖች በመያዝ የተሳኩ ጊዜያትን አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዲላ ላይ ረጅም ዓመታትን የሴት እግር ኳስ ፕሮጀክት በግሉ በመክፈት በ90ዎቹ አጋማሽ ወደ ስልጠና የገባ ሲሆን የጌዲኦ ዞን እና የደቡብ ክልል የሴት ምርጥ ቡድኖችን በመያዝ በተደጋጋሚ ቻምፒዮንስ በመሆን ይታወቃል፡፡

በመሐል የጌዴኦ ዲላ የወንዶች ቡድን በመያዝ ከአንደኛ ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ካሳደገበት 2008 ውጪ ረጆሙን ጊዜ እስከ ዘንድሮ የውድድር ዓመት ድረስ የጌዴኦ ዲላ የሴቶች ቡድንን በማሰልጠን ላይ የሚገኘው እንዳልካቸው በህንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2022 የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከዩጋንዳ ጋር ለሚጫወተው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ስለመመረጡ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ከሰሞኑ መታዘብ እንደቻለችው አሰልጣኝ እንዳልካቸው የኢትዮጵያ የሴቶች ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎችን በሀዋሳ ተገኝቶ ሲመለከት የነበረ ሲሆን ነገ አልያም ከነገ በስቲያ የመረጣቸውን ተጫዋቾች ፌዴሬሽኑ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡