​ሪፖርት | የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ተጋርቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከደቂቃዎች በፊት በተጠናቀቀው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ የማሸነፍ ጉዞ በአቻ ውጤት አቁሟል።

አምስት ተከታታይ ድሎችን አድርገው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወልቂጤ ከተማን አራት ለምንም ከረቱበት የመጨረሻ ጨዋታ አንድም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከሽንፈት በኋላ ወደ ድል የተመለሱበትን ውጤት ባሳለፍነው ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ ያገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ አንድ ተጫዋች ለውጠዋል። በዚህም የቡድኑ አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ሚካኤል ጆርጅን አሳርፈው ኤፍሬም ዘካሪያንስ በመጀመሪያ አሰላለፍ አካተዋል።

ሚዛናዊ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የግብ ማግባት ሙከራ ለማስተናገድ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ፈጅተውበታል። በእንቅስቃሴ ደረጃም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሲጥሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በረጃጅም ኳሶች ሦስተኛው የሜዳ ሲሶ ላይ ለመድረስ ሞክረዋል። ጨዋታውም የመጀመሪያ ሙከራ በ17ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከርቀት ወደ ግብ በላከው ኳስ ተስተናግዷል። ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በቀኝ መስመር ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሄደው በባዬ ገዛኸኝ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ባዬ ከደቂቃ በኋላም የተከላካዩ ምኞት ደበበን ስህተት ተጠቅሞ ሌላ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥሮ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሮ ነበር።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመግባት የጣሩት ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው አድርገው ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። ሀዲያዎችንም ወደ ራሳቸው ሜዳ እንዲመጡ እየጋበዟቸው የሚታወቁበትን ቀጥተኛ ኳስ ከተከላካይ ጀርባ ለመላክ ጥረው ሁለት እጅግ አደገኛ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በዚህም ከውሀ እረፍት መልስ አቤል ያለው ከወደ ቀኝ ባደላ የሜዳ ክፍል በረጅሙ የተላከውን ኳስ መጀመሪያ መትቶት የግብ ዘቡ መሳይ አያኖ ሲመልሰው ከደቂቃ በኋላ የደረሰውን ሁለተኛ ኳስ ደግሞ ለመጠቀም ሲጥር ተከላካዮች ጫና አብዝተውበት ኳሱን ከዒላማ ውጪ ሰዶታል። በጨዋታው ጅማሮ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር መልሰው ያገኙት ሀዲያዎች በ37ኛው ደቂቃ የተከላካይ አማካዩ ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት አርክሮ በመታው ነገርግን ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ በድንቅ ሁኔታ ባዳነው ኳስ ለግብ ቀርበው ነበር። ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተው የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሁለት አስገዳጅ የተጫዋች ለውጦችን ያደረጉት ሀዲያዎች የጊዮርጊስን ጠንካራ ጎን በማክሸፉ ረገድ ተዋጥቶላቸው ጨዋታውን ቀጥረዋል። በጥሩ እና ፈጣን የኳስ ቅብብል የጊዮርጊስ የግብ ክልል ተገኝተውም በ51 እና 53ኛው ደቂቃ በፍቅረየሱስ እና ባዬ አማካኝነት ሉክዋጎን ፈትነዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ኳሱን የግላቸው አድርገው የተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ የጣሩት ጊዮርጊሶች በአማካይ እና አጥቂ ቦታ ላይ ለውጦችን በማድረግ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። አቤልን ቀይሮ የገባው ቸርነትም በ66ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በአስቆጪ ሁኔታ አመከነው እንጂ ቡድኑን መሪ የሚያደርግ አጋጣሚ ነበር።

የጊዮርጊስ ግብ ለማስቆጠር ነቅሎ መውጣትን እንደ ግብ ምንጭነት ለመጠቀም የጣሩት ሀዲያዎች ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸውን ከተከላካይ ጀርባ እንዲገኙ በማድረግ ግብ ለማግኘት አስበዋል። በሁለተኛው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት የአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ተጫዋቾች ፍሬያማ ባይሆኑም ተጭነው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥረዋል። በተለይ በፈጣን ሽግግር በ86ኛው ደቂቃ አማኑኤል ተቀይሮ ከገባው አላዛር ጋር አንድ ሁለት ተጫውቶ የተቀበለውን የመጨረሻ ኳስ በስል አጨራረስ ከመረብ ጋር ለማዋሀድ ዳድቶ መሳይ አምክኖበታል። ጨዋታውም ግብ ሳይስተናገድበት 0-0 ፍፃሜውን አግኝቷል።

አንድ ነጥብ የተጋሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና በቅደም ትከተል 26 እና 17 ነጥቦችን በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።