​ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚገመተውን ጨዋታ እንዲህ ቃኝተነዋል።

አንድም ጨዋታ እስካሁን በሊጉ ያልተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት በአስተማማኝ ሁኔታ ተደላድሎ ለመቀመጥ እና በአሸናፊነት ለመዝለቅ ነገ ከሀዲያ ሆሳዕና ቀላል የሚባል ፈተና እንደማይጠብቀው ይታሰባል። 

በነጥብ ፣ ብዙ ግቦችን በማስቆጠር እና ጥቂት ግቦችን በማስተማገድ የሊጉ መሪ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ ምርጥ ብቃት ላይ ያለ ይመስላል። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ የሚገኙት ተጫዋቾቹ ደግሞ ምርጥ ብቃት ላይ መገኘታቸው እየጠቀመው ይገኛል። ኳስን የሚቆጣጠር ቡድን ሲገጥመው ከኳስ ውጪ በመሆን በአደገኛ ቦታዎች ኳስ እየቀማ ተጋጣሚ ሳይደራጅ በቀጥተኛ አጨዋወት ግብ ለማግኘት የሚጥር ሲሆን ለኳስ እምብዛም ፍላጎት የማያሳይ ቡድን ሲገጥመው ደግሞ ድርሻውን ራሱ ወስዶ በፈጣን ቅብብሎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክራል። በዋናነት ደግሞ ዘንድሮ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ የመጫወት ዕድል ያገኙት ሦስቱ የፊት መስመር አጥቂዎች ርህራሄ ቢስ ሆነዋል። ቡድኑ ካስቆጠራቸው 20 ጎሎች ላይም ኦሮ-አጎሮ፣ አማኑኤል እና አቤል 16ቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ (በማስቆጠር እና አሲስት በማድረግ) በማድረግ የፊት መስመሩን ስል አድርገዋል። የነገ ተጋጣሚያቸው ሀዲያ ደግሞ አብዛኛውን ጨዋታዎች በአምስት ተካላካዮች የሚቀርብ ስለሆነ በማጥቃት ሲሶ ላይ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው ያሰጋል። ይህንን ተከትሎም አንድ አንድ ግብ በስማቸው ያላቸውን የመስመር ተከላካዮች ሱሌይማን እና ሔኖክን ጨምሮ ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን ወደ ሳጥን የሚያደርጉ (Late Runner) የአማካይ ተጫዋቾችን በማበርከት የቁጥር ክምችቱን ማመጣጠን ይገባቸዋል።

እንዳልነው ቡድኑ በ12 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ማስተናገዱ ብቻ ጠንካራ የኋላ መስመር እንዳለው የሚጠቁም ቢሆንም ከአራቱ ጎሎች ደግሞ ሁለቱን ብቻ በክፍት ጨዋታ ማስተናገዱ (ሁለቱ በፍፁም ቅጣት ምት ነው) ምን ያህል ጠጣራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት እንደሆነ ያሳብቃል። በተለይ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ግብ አለማስተናገዱ እና በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዲደረግበት አለመፍቀዱ ለሀዲያ ሆሳዕና የቤት ሥራዎችን የሚያበዛ ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን ፈጣኖቹን የሀዲያ አጥቂዎች ከተከላካይ ጀርባ እየተገኙ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የማያመነቱ ስለሆነ የፈረሰኞቹ ተከላካዮች ሊዘናጉ አይገባም።

ከዓምና ጀምሮ በተከታታይ 14 የሊጉ ጨዋታዎችን ያልተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና በአሸናፊነት ለመዝለቅ እና በደረጃ መሻሻል ለማምጣት ብርቱ ፉክክር ነገ እንደሚገጥመው እሙን ነው።

ከወልቂጤ ከተማ ጋር በጣምራ እኩል አራት አራት ጨዋታዎችን ተሸንፎ፣ አሸንፎ እንዲሁም አቻ ወጥቶ አስረኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዲያ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የወጣበት ፍልሚያ የለም። በአማካይ ለሁለት የተጠጋ ግቦችንም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያስቆጠረው ስብስቡ ታሳቢ በተደረጉት ጨዋታዎች ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ማምከኑም ይታወቃል። ይህ ደግሞ ቡድኑ በተጋጣሚ ሳጥን የመድረስ ችግር እንደሌለበት በትንሹም ቢሆን ምስል ይሰጠናል። ይህ ቢሆንም ግን ከላይ እንደገለፅነው የሊጉን ምርጡን የተከላካይ ክፍል ባለቤት የሆነውን ጊዮርጊስ ነገ ስለሚገጥሙ ከመቼውም በላይ አጋጣሚዎችን በጥራት መፍጠሪያ መፍትሔ ቀይሰው ጨዋታውን ሊቀርቡ ይገባል። በተለይ ደግሞ በፈጣን ሽግግሮች እንዲሁም በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት እየተጠቀሙ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት መታተር የግድ ይላቸዋል።

በወራጅ ከጠናው ግርጌ ከሚገኙት ሰበታ እና ጅማ ውጪ በርካታ ግቦችን ያስተናገደ ሁለተኛው ክለብ የሆነው ሀዲያ (ከድሬ ጋር እኩል 14) ለማጥቃት ሰው ሜዳ ደርሶ ኳስ በሚያጣበት ሰዓት አስተማማኝ የመከላከል ቅርፁ ላይ ለመሆን የሚፈጅበት የሽግግር ጊዜ አንዳንዴ የረዘመ ነው። ይህ ደግሞ ፈጣን የአጥቂ መስመር ላለው ጊዮርጊስ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ስለሆነ በሽግግሮች ወቅት ቦታዎችን በቶሎ መዝጋት አለባቸው። ከዚህ ውጪ በአምስት ተከላካዮች እንደሚጫወት የሚታሰበው የቡድኑ የኋላ መስመር በራሱ ሜዳ ችምችም ብሎ ሲከላከል በክፍት ጨዋታም ሆነ በቆመ ኳስ እምብዛም በቀላሉ የሚፍረከረክ አለመሆኑ ለጊዮርጊስ ተጫዋቾች ፈተና የሚሆን ይመስላል።

ፈረሰኞቹ አዲስ ግደይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ቢመለስላቸውም የመሰለፍ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተመላክቷል። በአንፃሩ ከነዓን ማርክነህ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ጨዋታ አይኖርም። ከቤራዎቹ ደግሞ አስቻለው ግርማን ከቤተሰብ ሀዘን እንዲሁም ኤፍሬም ዘካሪያስን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ በተመሳሳይ ጉዳት እና የቤተሰብ ጉዳይ የነበረበት መላኩ ወልዴ መሰለፉ እስካሁን እርግጥ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።

ይህንን ጨዋታ ዋና ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ከመስመር ረዳት ዳኞቹ ሸዋንግዛው ተባበል እና ደረጄ አበራ እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ተፈሪ አለባቸው ጋር በመሆን እንደሚመሩት ታውቋል።


የእርስ በእርስ ግንኙነት 

– ቡድኖቹ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቴ ሀዲያ ሆሳዕና አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸው አንዴ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በእነዚህ ጨዋታዎች ጊዮርጊስ አምስት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለት ግቦችን አስመዝግበዋል።


ግምታዊ አሠላለፍ 


ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – በረከት ወልዴ

አቤል ያለው – እስማኤል ኦሮ-አጎሮ – አማኑኤል ገብረሚካኤል


ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

መሳይ አያኖ

ቃለዓብ ውብሸት – ፍሬዘር ካሳ – ሄኖክ አርፊጮ

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ኢያሱ ታምሩ

ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ