ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ መከላከያ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ13ኛውን ሳምንት ሦስተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አይተናል።

በሊጉ ጥቂት ግቦችን ከሚያስቆጥሩ ቡድኖች መካከል የሆኑት አዳማ እና መከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ በጥቂት የግብ ልዩነት የሚጠናቀቅ ይመስላል። ከሰበታው ድል በኋላ ከኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ አንድ አንድ ነጥቦችን ያሳካው አዳማ ከተማ 66 በመቶው የሚሆነውን ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቆ መከላከያን ያገኛል። በአንፃሩ መከላከያ እስካሁን ካድረጋቸው ጨዋታዎች በአጋማሹ ለሽንፈት ተዳርጎ ወደነገው ጨዋታ ያመራል።

በሊጉ ሁለተኛ ጠንካራ የመከላከል ሪከርድ ያለው አዳማ ከተማ የመከላከያን ጥቂት የፈጠራ ምንጮች ለመግታት ወሳኝ ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞንን ማጣቱ ሊፈጥበት ከሚችለው ክፍተት ባለፈ ግለሰባዊ ስህተቶች እንዳይደጋገሙ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል። በድኑ አማካይ ክፍል ላይ ካለው የሰራተኝነት ደረጃ አንፃር ስንመለከተውም ተጋጣሚው ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ወደ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲያደላ ማስገደድ የሚችል ይመስላል። ከዚህ በተጨማሪ በጥሩ የመከላከል እና የማጥቃት ተሳትፎ የተመለከትናቸው የመስመር ተከላካዮቹ ደስታ እና ጀሚል የጦሩ ተመሳሳይ ቦታ ተሰላፊዎች እምብዛም ከራሳቸው ሜዳ የማይወጡ ከመሆናቸው ጋር በተገናኘ የተሻለ የማጥቃት ኃላፊነት እንደሚጣልባቸው ይጠበቃል።

ከመከላከሉ በተቃረነ ሁኔታ ደካማ የማጥቃት ቁጥሮች ያልሏቸው አዳማዎች ከፊት ዳዋን መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ተጨማሪ ስጋት ይመስላል። በመሆኑም ከላይ እንዳነሳነው ከመስመር ተከላካዮቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ሚና በተጨማሪ በመስመር አጥቂዎቹ ወደ ውስጥ እየጠበበ የሚሄድ የቡድን መናበብን የሚጠይቅ ጥቃት የዳዋን ክፍተት መሸፈን አስፈላጊው ይሆናል። በዚህ በኩል ሌሎቹ የቡድኑ አጥቂዎች ምን ዓይነት ቀን ይኖራቸዋል የሚለው ተጠባቂ ሲሆን የመሀል ክፍል ተጫዋቾቹም ለሳጥን ቀርበው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አጋዥ እንደሚሆን ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ወደ እነሱ ደረጃ የቀረበ የመከላከል ቁጥር ያለው መሆኑ ግን በግብ ፊት ሁኔታዎች ይበልጥ እንዲከብዱባቸው ማድረጉ የሚቀር አይሆንም።

በተጨዋች እና አደራረደር ምርጫው እንዲሁም በሚና አሰጣጡ ተለዋዋጭነትን የሚከተለው መከላከያ በየጨዋታው ግቦችን በሚፈልገው መጠን ሲያገኝ አይታይም። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከቆመ ኳስ መነሻነት ሦስት ግብ ካስቆጠረበት የወልቂጤ ጨዋታ በቀር በሌሌቹ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሲከብደው ይታያል። ለሁኔታው የቁልፍ ተጫዋቾች መጎዳት እና የተሰላፊዎች ልምድ ማነስ እንደምክንያትነት ቢቀርብም የግብ ዕድል የመፍጠሪያ ታክቲካዊ ጉዳዮችም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ከነገው ተጋጣሚው የመከላከል ጥንካሬ አንፃርም ከመጀመሪያው ምክንያት ይልቅ ሁለተኛው ትኩረትን ይስባል።

ለአብነት የመጨረሻውን የድቻን ጨዋታ ብንወስድ ተለዋዋጭ የሆነው የቡድኑ አደራደር 4-4-2ን ምርጫው ሲያደርግ የጨዋታ ፍሰቱ ግን ከቀጥተኝነት ይልቅ ከአደራደሩ ጋር በማይጣጣም መልኩ ለኳስ ቁጥጥር የቀረበ ነበር። በዚህ ላይ የቡድኑ ዋና የፈጠራ ምንጭ የሆነው ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ሲነሳ በሜዳው ቁመት የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ያጣመረው ወላይታ ድቻ ተጫዋቹ ከኳስ ጋር ሲገናኝ አንድ አማካይ ጭምር ወደሱ በማቀርብ አንድ ለ ሦስት በሆነ ብልጫ እንቅስቃሴውን ሲገታው ይታይ ነበር። ነገም ጦሩ የግብ ዕድሎችን በብዛት የመፍጠሪያ የተሻለ የጨዋታ ስትራቴጂ ይዞ ካልተገኘ ከድቻም በላይ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆነው አዳማን ለመፈተን የቆሙ ኳሶች እና የርቀት ሙከራዎች ላይ ብቻ ተስፋውን እንዲጥል የሚገደድ ይመስላል።

ሁለቱ ቡድኖች በጉዳት የሚያጡት አዲስ ተጫዋች ባይኖርም አዳማ ከተማዎች ዳዋ ሆቴሳን እና ሚሊዮን ሰለሞንን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ምክንያት የማይጠቀሙ ሲሆን የመከላከያው ገናናው ረጋሳም ሙሉ ለሙሉ አላገገመም።

ይህ ጨዋታ በአዳነ ወርቁ የመሀል ዳኝነት አመራር ሲሰጥበት ፋሲካ የኋላሸት እና ዘሪሁን ኪዳኔ በረዳትነት እንዲሁም ዛሬ ምሽት የተደረገው የድሬዳዋ እና ባህር ዳርን ጨዋታ የመሩት በላይ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡደኖች በአጠቃላይ በሊጉ 27 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ በ8 መከላከያ በ7 ጨዋታዎች ሲያሸንፉ በ12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ በእነዚህ ግንኙነቶች መከላከያ 19 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ 22 አስቆጥሯል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – አሚን ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ኢብራሂም መሀመድ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – አዲሱ አቱላ

ሰመረ ሀፍተይ – ቢኒያም በላይ – ግሩም ሀጎስ

ኦኩቱ ኢማኑኤል