​የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-1 ጅማ አባ ጅፋር

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጅማ አባ ጅፋር ሦስተኛ ድሉን ካሳካበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ውጤት ለመቀየር ከቀጥተኛ ኳስ ውጪ ሌላ አማራጭ ስላለመጠቀማቸው

“በመጀመሪያ በሁለታችን መሀል ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። መሀል ሜዳውን ካልተቆጣጠርን በቀር ልንቸገር እንደምንችል ተናግሬያለሁ። የዕለቱ ኮከብ የነበሩትም ዳዊት እና መስዑድ ናቸው። እነሱን ለመቆጣጠር የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች በጣም ተቸግረናል። ያም ሆኖ እነሱ በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ነበሩ ፤ እኛ ደግሞ ወደ ጎል በመድረስ የተሻልን ነበርን። የማይሳቱ ጎሎች ናቸው ሲሳቱ የነበሩት እና ብዙ የጎል አጋጣሚዎች አግኝተናል። እንደዚህ ዓይነት ቡድንን መጀመሪያ በጎል ካላወረድከው ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር በራስ መተማመናቸው እያደገ ይመጣል እና በአጠቃላይ ሲታይ በመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ላይ ሁሉን ነገር መጨረስ የምንችልባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል። ምክንያቱም የተገኙ አጋጣሚዎችን መጠቀም መቻል አለብን። በራሳችን ድክመት የተገኘ ውጤት ነው ማለት እችላለሁ።

ለተጋጣሚ ዝቅ ያለ ግምት ስለመስጠት

“ያንን እንኳን ማለት አልችልም። ምክንያቱም ተነጋግረናል። ስለተጋጣሚያችንም ስላለፈው ደካማ ጎናችንም ከልምምድ ውጪ እየተወያየን ነው የምንመጣው። በእርግጥ ጎል ከገባ በኋላ ወደ አላስፈላጊ ብስጭት እና ንዴት ከታክቲክ ዲስፕሊን ውጪ ሲሆኑ አይቻለሁ። በዕረፍት ይህንን ለማስተካከል ፎርሜሽናችንን ቀይረን የተከላካይ ቁጥር ቀንሰን ለማጥቃት ሞክረናል። ዞሮ ዞሮ የተወሰደብንን ብልጫ ለማስመለስ ከፍተኛ ትግል አድርገናል። ባለመረጋጋት እና ጥድፊያ በበዛበት እንቅስቃሴ ውጤቱን አጥተናል። ስለዚህ በአስቸኳይ ለማረም መዘጋጀት አለብን ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ከፊታችን ብዙ የራቁ አይደሉም ከኋላ ያሉትም እየተጠጉን ነው። ውድድሩ ጥሩ እየሆነ ነው ያለው እና ድክመታችንን ማረም የውዴታ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ። ”

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው እና ውጤቱ

” ውጤቱ ለመንደርደር ትልቅ ጉልበት ይሆነናል። በታክቲክ ዲስፕሊን ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነበር። እኛ ላይ ብዙ ጎሎች ተሞክረዋል። ለዚህ ደግሞ የታዳጊው ግብ ጠባቂያችን አስተዋፅዖ ትልቅ ዋጋ ነበረው። በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግነው አላልፍም። ይህንን ዕድል ያመቻቸልኝ ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴው ነው። ወጣቶችን ለማምጣት ሳስብ ቦርዱ ሙሉ ነፃነት ነው የሰጠኝ። ለሀገርም ተስፋ የሚሰጥ ነው። በዚህ አጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ወጣቶችን ስለሰጡን እግረ መንገዴን ሳላመሰግናቸው አላልፍም።

ጅማ ስለመትረፉ

“ይህን ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የጠየቃችሁኝ። በእርግጠኝነት ይተርፋል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ያለን ልዩነት የሁለት ጨዋታ ነው። እኛ ብዙ ዋጋ የከፈልነው ሀዋሳ ላይ ነው። አንደኛ የማታ ጨዋታ ነው። ልጆቹ ወጣቶች ናቸው መብራት ሲያዩ የገባብን ጎሎች አሉ። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል። በቀጣይ ያለን የድሬዳዋ ጨዋታ ሁለት ጨዋታ ነው። ታክቲካል ዲስፕሊን የሚጠይቅ ጨዋታ ነው። ኳስ በያዘ ሳይሆን እንዴት ልናሸንፍ እንደምንችል ከልጆቻችን ጋር ተነጋግረን የሚቀሩንን ጨዋታዎች በድል ጨርሰን ድሬዳዋን አመስግነን እንመለሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ስለተጋጣሚ አቀራረብ እና ስለጫና

“ተጋጣሚያችን እንዲህ ሊጫወት እንደሚችል አስበን ነው ተጫዋቾቻችንን አሰላለፍ ውስጥ የከተትነው። ‘ምንያህል ተግባራዊ አድርገነዋል ? ምን ያህል ተቆጣጥረነዋል ?’ ራሱን የቻለ ምክንያት ቢኖረውም የምንፈልገውን አጨዋወት ነው ሙሉ ለሙሉ የተጠቀሙት በዚህ ደግሞ ዕድለኞች ነን ብዬ አስባለሁ። ከዛ ውጪ ተጫዋቾቼ ላይ ጫና አለ። እኔ እንኳን በዚህ ቆዳዬ የደነደነ ነው። ተጫዋቾቼ ግን ልጆች ናቸው ይጨነቃሉ። በእነሱ ቦታ ሆኜ የማስበው ነገር ትንሽ ይረብሸኛል። ከዛ ውጪ ግን ልምድም የሚባለው እነዚህን ነገሮች ሁሉ ተቋቁሞ መሄድ ነው። እኔ እንደውም በጣም የሚደንቀኝ አመራሩ አለማባረሩ ነው። ምክንያቱም ያጣሁት ውጤት በጣም ብዙ ነው። በትዕግስት መጠበቃቸው ይደንቀኛል ፤ እኔ ብሆን አላደርገውም። ግን እነሱ ደግሞ በእኔ ላይ ዕምነት መጣላቸው ቡድኑን ቆም ብዬ እንድሰራ ፣ ወጣቶችን በአግባቡ እንድጠቀም አድርጓል። ፍሬውንም በሂደት እናየዋለን ብዬ አስባለሁ።”