​ሽመልስ በቀለ ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን አድርጓል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በግብፁ ክለብ አል-ጎውና የሚገኘው የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ በቀለ ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን ከደቂቃዎች በፊት አከናውኗል።

የግብፅ ከፍተኛው የሊግ ዕርከን ውድድር ባለንበት ሳምንት የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን እያከናወነ ይገኛል። ያለፉትን ስምንት ዓመታት በግብፅ ሊግ በመጫወት የእግርኳስ ህይወቱን እየቀጠለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ሽመልስ በቀለ በካሜሩን አስተናጋጅነት በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት በሚሰራበት ወቅት የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት አስተናግዶ ውድድሩ ላይ ተሳትፎ ሳያደርግ ቀርቶ እንደነበር ይታወሳል።

ከአህጉራዊ ውድድር በኋላ ወደ ክለቡ የተመለሰው ተጫዋቹም ከሳምንታት በፊት ከጉዳቱ እያገገመ ልምምድ መስራት የጀመረ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንትም የአቋም መለኪያ ጨዋታ ላይ ተካፍሎ ራሱን ለጨዋታ አዘጋጅቶ ነበር። ክለቡ አል-ጎውና ከኢስማዒሊ ጋር ከደቂቃዎች በፊት የአስረኛ ሳምንት ጨዋታ አከናውኖ በካሊድ ካማር ብቸኛ ግብ ሲያሸንፍ ተጫዋቹ ተቀይሮ በመግባት በጨዋታው ላይ ተሳትፏል።

71ኛው ደቂቃ ላይ መሐሙድ ሻብራዊን ቀይሮ የገባው ተጫዋቹም እስካሁን አራት ጨዋታዎችን (ሁለቱን ተቀይሮ በመግባት) በሊጉ አከናውኖ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።