ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ኮቪድ ያንዣበበት የነገውን ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

በአንድ በኩል ከላይ እና ከታች ባለው ፉክክር ላይ ለሁለቱም የመዲናዋ ተጋጣሚዎች ወሳኝ የሆነው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን እንደሚያስመለክተን ሲጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ ከመሸ የተሰሙ የኮቪድ ዜናዎች ጥላ አጥልተውበታል። አሁን ላይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ቦታውን ለድሬዳዋ አስረክቦ ከሁለተኛው ዙር መጀመር በፊት ከአደጋው በመጠኑ ፈቀቅ ለማለት የነገው ጨዋታ ሙሉ ውጤት ያስፈልገዋል። ሊጉን እየመራ ውድድሩን ማጋመሱን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስም የነጥብ ልዩነቱን አስፍቶ ብቸኛው ባለ ሠላሳ ቤት ባለነጥብ በመሆን ቀጣዩን ዙር በምቾት ለመጀመር ማሸነፍ ያስፈልገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የጨዋታ ዕቅድ እና አተገባበሩ በአጠቃላይ የሚኖረውን የዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ዓይነት የሚወስነው ይመስላል። ቡድኑ በጥልቀት በራሱ ሜዳ ላይ በመቆየት የኳስ ቁጥጥሩን ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚተው ከሆነ እና ይህንንም በጥሩ የትኩረት ደረጃ መተግበር ከቻለ የሊጉ መሪዎች በሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ የገጠማቸው ፈተና ዳግም ሊያገኛቸው ይችላል። አዲስ አበባዎች በተለመደው አኳኋን ኳስ ይዘው እና የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ፍጥነት ለመጠቀም ካሰቡ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፈጣን ሽግግር ከተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የተሻለ ዕድልን ያገኛል። በሁለቱም መንገዶች ግን ለአዲስ አበባ ፈታኝ የሚሆነው እጅግ የሚዋዥቅ አቋሙ ነው።

በሰሞንኛ ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ ላይ አምስት ግብ ያስቆጠረው አዲስ አበባ እና እምብዛም ጠንካራ ባልነበረው ሲዳማ ቡና 1-0 የተሸነፈው አዲስ አበባ መካከል የነበረው የአቋም ልዩነት እጅግ የተራራቀ ነበር። ከዚያ ወደ ኋላ ከሄድን ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና የተጋነነ ግምት ሰጥቶ በጥልቀት ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት አስቦ በገባበት ጨዋታ ያሳየው እጅግ ደካማ አፈፃፀምን መከላከያ እና ፋሲል ከነማን ሲያሸንፍ ካሳየው በፈጣን የማጥቃት ዕቅድ ውስጥ የሚመደብ ያልታሰበ ብቃት ጋር ስናስተያይ ልዩነቱን እንረዳዋለን። የነገው ቡድንም ከጨዋታ ዕቅድ ባለፈ አተገባበሩ በየትኛው ፅንፍ ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ጨዋታውን የመወሰን አቅሙ ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን።

በሦስት ጨዋታዎች አስር ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ብቻ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚዎቹ አቀረረብ እየተወሰነ እንደሚገኝ መናገር ይቻላል። ቡድኑ በቀጥተኛ አጨዋወት ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚያደርሳቸውን ኳሶችም ሆነ ከራሱ ሜዳ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ይዞ የሚወጣቸውን ኳሶች ወደ አደጋ መቀየር ሲሳነው አይታይም። እንደመጨረሻ ተጋጣሚዎቹ ክፍተቶችን ዘግተው ለሚቀርቡ ቡድኖች መላ የሚሆን ውጤታማ ዕቅድ ይዞ መቅረብ ግን የነገውም የቤት ስራው ሊሆን ይችላል። ነገ ደግሞ በርከት ያሉ ተጫዋቾቹን በኮቪድ ምክንያት እንደሚያጣ መሰማቱ ተፈላጊውን ምላሽ ለመስጠት አልያም የቀደመውን የመልሶ ማጥቃት ጠንካራ ጎኑን ዳግም በነበረው ልክ ለመተግበር በሚኖረው የተጫዋቾች አማራጭ ላይ እንዲወሰን ይገደዳል።

በጥቅል ስንመለከተው ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ተሳትፎ ከፍ በማድረግ የተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ ላይ የሜዳውን ስፋት አብዝቶ በመጥቀም ለግብ የመቅረብ ዝንባሌ እያሳዩ ያሉ አማካዮቹን እና የፊት አጥቂዎቹን በቅብብሎች ማገናኘት መፍትሄ ሊሆነው ይችላል። በአዲስ አበባ በኩል እንደ ቡናው ጨዋታ ለተጋጣሚ የተጋነነ ግምት መስጠት የሚያዋጣ ባይመስልም ቡድኑ ግለሰባዊ ስህተቶችን መቀነስ እና በቀላሉ ግብ የማያስተናግደው ተጋጣሚውን በሽግግሮች ወቅት በሚኖሩ ቅፅበቶች በቅጥተኛ ኳሶች ለማግኘት ማቀድ የተሻለው አማራጩ ሆኖ ይወሰዳል።

በነገዎቹ ተጋጣሚዎች ዙሪያ ከተሰሙ እና በቁጥር በርካታ ከሆኑ የኮቪድ ኬዞች ውጪ በጊዮርጊስ በኩል የከነዓን ማርክነህ ለጨዋታው መድረስ ሲያጠራጥር ረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው አዲስ ግደይ መመለስ ተምቷል። በአዲስ አበባ ስብስብ ውስጥ ደግሞ የሽዋስ በለው ብቻ በጉዳት ጨዋታው ያልፈዋል።

ጨዋታው በበላይ ታደሰ የመሀል ዳኝነት ሲከናወን በረዳትነንት አበራ አብርደው እና ዘሪሁን ኪዳኔ በአራተኝነት ደግሞ እየሱ ፈንቴ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2009 የውድድር በተገናኙባቸው ብቸኛ ጨዋታዎች በቅድሚያ 1-1 ሲለያዩ በሁለተኛው ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ማሸነፍ ችሏል።

* ከላይ እንደገለፅነው በክለቦቹ ያለውን የኮቪድ-19 ኬዝ ታሳቢ በማድረግ በዚህ ሳምንት ግምታዊ አሰላለፍ ማውጣት አልቻልንም።