የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 13ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ መሪው ቡራዩ የተሸነፈበት እና ቤንች ማጂ ቡና ወደ መሪነት የተጠጋበት ድል ተመዝግቧል።

በባቱ ሼር ሜዳ እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ለ ውድድር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፀሀፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልስጣኝ አስራት አባተ እና የጅማ አባ ጅፋር ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ታድመው ተመልክተናል።

በሁለተኛው ዙር እጅጉን መሻሻል ያሳዩት ቤንች ማጂ ቡናዎች ከመሪዎቹ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም ከንባታ ሺንሺቾ ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ ያስፈልገው የነበረው ጨዋታ በቤንጂ ማጂ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ4፡00 ላይ የጀመረው ጨዋታ በፌዴራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ሲመራ በሁለቱም አጋማሾች ቤንች ማጂ ቡናዎች የተሻሉ እንደነበሩ መመልከት ይቻላል፡፡ በጨዋታው ጅማሮ ኳስን ወደ 16 ከ50ው በመጣል የቤንች ማጂ ቡናን ግብ ለመፈተሽ ሙከራ ያደረጉት ሺንሺቾዎች በ5ኛው ደቂቃ በናሆም አዕምሮ እንዲሁም በ12ኛው ደቂቃ በዮሐንስ ተሰማ ግልፅ የግብ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ቀስ በቀስ ወደ እንቅስቃሴ የተመለሱት ቤንች ማጂዎች በመሀል ሜዳ ላይ በማንሸራሸር ወደ ቀኝ መስመር በብዛት ኳስን በመጣል ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ኤፍሬም ታምሩ በ14ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የሽግግር አጨዋወት የተገጣሚቸውን ግብ ለመፈተሽ ያደረገው ጥረት በሺንሺቾ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች ከሽፏል። ብዙም ሳይቆይ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ማዕዘን ምት ማግኘት የቻሉት ቤንቺ ማጂዎች ኳስ የግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቷ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ቀድሞ አቋሙ የተመለሰው ወንድማገኝ ኬራ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ከግቡ መቆጠር ሁለት ደቂቃ በኋላ በግራ መስመር ወደፊት የተጣለው ኳስ የሺንሺቾዎች ስህተት ታክሎበት ወንድማገኝ ኬራ በፍጥነት ወደ ክልሉ በመግፋት በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ዘላለም በየነ አሻግሮለት የቤንች ማጂን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቋጠር በኋላ ተረጋግተው መጫወት የቻሉት ቤንች ማጂዎች አሰልጣኝ ማሀመድ ኑር የሚታወቅበትን አጭር ኳስ ቅብብል ለማድረግ ጥረት ሲደርጉ ተስተውሏል። በእንቅስቃሴ ብልጫ የተወሰደባቸው ሺንሺቾዎች ግን ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያስመልክቱ ቀርተዋል። በ44ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አካሉ አቲሙ ከርቀት አክርሮ ሲመታ ለቤንች ማጂ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሮ በቤንች ማጂ የበላይነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ግብ ፍለጋ የታተሩት ሺንሺቾዎች በናሆም አዕምሮ እና አሸናፊ ዋሎ አማካይነት የቤንች ማጂ ቡናን ግብ ክልል ለመፈተሽ ሙከራ ሲደርጉ አርፍደዋል። ሆኖም ወደፊት ተጠግተው የሚጫወቱት ሺንሺቾዎች ነቀለው በወጡበት ሰዓት በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ በመጠቀም የፊት መስመር አጥቂው ወንድም አገኝ ኬራ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሯል። በድጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ቤንች ማጂዎች በወንድምአገኝ ኬራ ፣ ቶስላች ሳይመን እና ዘላለም በየነ የግብ ሙከራ ቢደርጉም በለስ ሳይቀናቸው ቀርቷል። በተቃራኒው ሺንሺቾዎች ልዩነቱን ለማጥበብ በተደጋጋሚ ጥረት ሲደርጉ ቆይተው በ80ኛው ደቂቃ ላይ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ድልነሳው ሽታይ የሺንሺቾን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላ ጨዋታው ሌላ ግብም ሆነ ተጨማሪ ትዕይንት ሳያስመልክተን በቤንች ማጂ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ8:00 ሰዓት ኮልፌ ከመመራት ተነስቶ ቂርቆስን አሸንፏል።  በቀድሞ የኢትዮጵያ ቡኣ ምክትል አሰልጣኝ አሠልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ የሚመራው ቂርቆስ ክፍለከተማ በሁለተኛ ዙር ውድድር ማራኪ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ይገኛል። አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾችን ያቀፈው ቡድኑ በ5ኛው ደቂቃ አቤል አክሊሉ አሥራት አሻግሬ በቀኝ በኩል ያመቻቸለትን ኳስ ለጥቂት ባያመልጠው ኖሮ ቀዳሚ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮ ነበር። በኳስ ቁጥጥር በልጠው የተገኙት ቂርቆሶች የተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ቢደርሱም የመጨረሻውን የሜዳ ሲሶ ስል መሆን አቅቷቸው ነበር። በተቃራኒው ኮልፌ ቀራኒዮዎች በረጃጅሙ የሚሻግሩ ኳሶችን ወደ አዳጋ ለመቀየር ቢያስቡም ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

ጨዋታው 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ግብ አስተናግዶ መሪ አግኝቷል። በዚህም ብሩክ አየለ ከአስራት መገርሳ የተቀበለውን ኳስ በግምት 18 ሜትር ርቀት ላይ በቀጥታ ከሳጥን ውጭ አክሮሮ በመምታት ቂርቆስን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ቂርቆሶች መቀዛቀዝ ሲታይባቸው ተጋጣሚያው ኮልፌዎች ቢነቃቁም ክፍተት ማግኘት ሳይችሉ አጋማሹ በቂርቆስ 1-0 መሪነት ተገባዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለት መልኮች የነበሩት ነበር። በአጋማሹ የመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ኮልፌዎች እጅግ የተሻለ በመንቀሳቀስ ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። በቅድሚያም በ48ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በቀጥታ አሸናፊ ገዛኸኝ በመታው ኳስ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ኮልፌዎች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን በፉዐድ መሐመድ አማካኝነት ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ነገር ግን በ64ኛው ደቂቃ አሸንፊ ያሳለፈለትን ኳስ ፉዐድ መሐመድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ቀድሞ ብቃታቸው የተመለሱት ቂርቆሶች የኮልፌ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ማገኛነት ሳይችሉ ቀርተዋል። ከውሀ ዕረፍት በኋላ በድጋሚ የተነቃቁት ኮልፌዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ኳሱን በመያዝ ሳጥን ውስጥ በመግባት አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ታይቷል። በተለይ በ79ኛው ደቂቃ እሱባለሁ ሙሉጌታ በዚሁ እንቅስቃሴ የተገኘውን አጋጣሚ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ዳግም አረኔ ያደነበት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር። በ84ኛው ደቂቃ ግን ፍሬያማ ሆነው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም እሱባለሁ ሙሉጌታ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ኮልፊን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። የአቻነት ግብ ፍልጋ ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው የተገኙት ቂርቆሶች በ92ኛው ደቂቃ አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ አስራት አሻግሬ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በኮልፌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በ10:00 የምድቡ መሪ ቡራዩ ከተማ በሰንዳፋ በኬ ሽንፈት አስተናግዷል። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አሰልቺ እና ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ የተመለከትን ሲሆን ረጃጅም ኳሶች እና አካላዊ ጉሽሚያዎችም በርክተው ነበር። ከጅምሩ የቡራዩን ግብ መፈተሽ የጀመሩት ሰንዳፋ በኬዎች በ12ኛው ደቂቃ ፎሳ ሰንዲቦ ከቡራዩ ግብ ጠባቂ ዓይናለም ብርሃኑ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሞክሮ በነበረው ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ዛኪ አብዱ ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ግብ የተቆጠረበት ቡራዩ ከተከላካይ ኋላ በሚሻገሩ ረጅጅም ኳሶች የሰንዳፋ በኬ የግብ ክልል እየደረሱ የአቻነት ግብ ፍለጋ ሲጥሩ የቆዩ ሲሆን በቶሎም ጥረታቸው ሰምሯል። በዚህም በ20ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት መለሰ አሻሞ ያሻገረውን ኳስ የሰንዳፋው ግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት ቴዎድሮስ ታደሠ በግንባሩ የቡራዩን የአቻነት ግብ አስቋጥሮል። በተመሳሳይ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደሜዳ የገቡት ሁለቱ ቡድኖች በረጅጅም ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደተጋጣሚያቸው ግብ ቢደረሱም የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ከሰንዳፋ በኬ ቅዱስ ተስፋዬ እንዲሁም ከቡራዩ ጫላ ቤንቲ ያደረሱት ጥቃት እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ከዕረፍት መልስም አዲስ ነገርን ለመመልከት የሚያስችሉ የጨዋታ ቅርፅ ለውጦችን ቡድኖቹ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይበልጥ ከመጀመሪያው አጋማሽ በበለጠ ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወተ ሲከተሉ ነበር። ይሁን እንጂ ሰንዳፋ በኬዎች በመጠኑም ቢሆን ኳስ ይዘው ለመጫወት ሞክረዋል። ሆኖም ጥቃት የሚፈፅሙት ወደ ቅዱስ ተስፋዬ አጋድለው በሚጣሉ ኳሶች ነበር። ይህ ጥረታቸውም በ60ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል። ተጫዋቹም በድጋሚ ከርቀት አክርሮ በመምታት ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮል። የምድቡ መሪ ቡራዩ የማጥቃት እንቅስቃሴን ከኋላ በሚላኩ ኳሶች መሰረት በማድረግ ቢንቀሳቀስም ውጤት ሳያገኝ ጨዋታው በሰንዳፋ በኬ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሉ በሁለተኛው ዙር የተዳከሙት ቡራዩዎች የምድብ መሪነታቸውን ቢቀጥሉም ከተከታዮቻቸው ያላቸው ልዩነት እየጠበበ ይገኛል።