የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ 13ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተከናወነ በሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የ13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተደምድመዋል፡፡

3፡00 ሲል ጅማ አባቡና እና ጉለሌ ክፍለ ከተማን ያገኛነው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ ይህንን ጨዋታ አቶ ኢሳይያስ ጂራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ አቶ አበበ ገላጋይ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም አሊሚራህ መሀመድ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ተገኝተው ታድመዋል፡፡

ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና መሀል ሜዳ ላይ በአመዛኙ እንቅስቃሴዎች በርክተው በታየበት በዚህ ጨዋታ በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ኳስን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ የጉለሌዎች የበላይነት መታየት የቻለበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ጉለሌዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጥቃት በመሰንዘር የበላይ ሆነው መታየት ቢችሉም ወደ ሳጥን ጠርዝ ሲደርሱ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ይታይባቸው ስለነበር። በ90 ደቂቃውም አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ መመልከት ሳንችል ያለ ግብ ፍፃሜውን አግተኝቷል፡፡

የምድቡ ሁለተኛ የቀኑ ጨዋታ በደቡብ ፖሊስ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች እርስ በእርስ ሜዳ ላይ ከሚታዩ ሽኩቻዎች እና ጉሽሚያዎች ውጪ የጠሩ አጋጣሚዎችን መመልከት ያልቻልን ቢሆንም በሂደት ግን የደቡብ ፖሊስ ቅርፁን የያዘ የጨዋታ መንገድ በተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን እንዲፈጥሩ ረድቷቸዋል፡፡ በዚህም 16ኛው ደቂቃ ላይ መኮንን ዮሴፍ በአንድ ሁለት ቅብብል የደረሰውን ኳስ በቀላሉ ወደ ግብነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ቢኒያም ሀብታሙ (ኦሼ) አድኖበታል፡፡

በዕለቱ ዳኛ ላይ በተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያንፀባርቁት ካልሆነ በስተቀር መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ብቻ ሲያደርጉ የታዩት አቃቂዎች አንድም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለማለፍ ተቸግረው በደንብ ታይተዋል፡፡ የግብ ዕድልን በተሻለ ለማግኘት የታተሩት ቢጫ ለባሾቹ 28ኛው ደቂቃ ላይ ይድነቃቸው ለማ ከቅጣት ሲያሻማ ምንተስኖት ታምሩ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ በድጋሚ ምንተስኖት ታምሩ በግምት ከ30 ሜትር ቦታ ላይ ከቅጣት አክርሮ መቶ ቢኒያም ሀብታሙ በሚገርም ብቃት ያወጣበት ሌላኛው የፓሊሶች ጥቃት ነበረች፡፡ አጋማሹ ሊጋመስ አንድ ደቂቃ ሲቀረው መኮንን ዮሴፍ ለደቡብ ፓሊስ ግብ ቢያስቆጥርም አስቀድሞ ተጫዋቹ በአቃቂ ተከላካይ ላይ ጥፋት በመፈፀሙ ግቧ ሳትፀድቅ ቀርታለች፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ልክ በመጀመሪያው አጋማሽ ደቡብ ፖሊስ ሲያሳዩ የነበረውን ተመሳሳይ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ ሂደት አስቀጥለው ሲታዩ በአንፃሩ አቃቂ ቃሊቲዎች በመልሶ ማጥቃት ያልተሳኩ የጨዋታ መንገዶችን ለመከተል ሲጥሩ ተንፀባርቋል፡፡ የደቡብ ፖሊሶች የሙከራ የበላይነትን አሁንም በዚህኛው አጋማሽ ተሽሎ የታየ ሲሆን በተደጋጋሚ ያገኙኟቸውን ዕድሎችን ግን በመጠቀሙ ረገድ ፍፁም ደካሞች ነበሩ፡፡ ሁለት ጊዜ ከማዕዘን በተሻማ ኳስ ተከላካዩ ሲሳይ በዳሞ በግንባር ገጭቶ በተመሳሳይ ሂደት የወጣበት እና 81ኛው ደቂቃ መኮንን ዮሴፍ ከመስመር አሻምቶ ምንተስኖት ታምሩ ከግብ ጠባቂው ቢኒያም ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ቢኒያም ልምዱን ተጠቅሞ ይዞበታል፡፡በተደጋጋሚ ብልጫን ወስደው ግብ ለማግኘት የተቸገሩት ፓሊሶች ኳስን ከመረብ ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው 0ለ0 ተጠናቋል፡፡


የካ ክፍለ ከተማን ከሶዶ ከተማ ያገናኘው የቀኑ ሶስተኛ የምድቡ ጨዋታ 10፡00 ሲል ጀምሯል፡፡ ሶዶ ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው አማካዩ ኃይለየሱስ ኃይሌ እና በቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ አላዛር ፋሲካ አማካኝነት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን በዚህኛው አደርገዋል። ገና በጊዜ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት አከባቢ ኃይለየሱስ ኃይሌ አክርሮ መትቶ የየካው ግብ ጠባቂ ኩን ሮች ድንቅ ብቃት ተመልሳ ወደ ማዕዘን ስትወጣ በድጋሚ ሲሻማ አላዛር ፋሲካ በግራ እግሩ ያለቀለትን የማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም በሚያስቆጭ መልኩ በግቡ ቋሚ ታካ ወደ ውጭ ወጥታለች። ሶዶ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጨማሪ የጠሩ ዕድሎችን መመልከት ሳንችል የቀረን ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው የካ ከእንቅስቃሴ እና ረጃጅም ኳሶችን ከመጣል በዘለለ ውጤት አልባ የሆነ የጨዋታ መንገድን በመከተላቸው ይህ ነው የሚባል የጎል አጋጣሚን ለመፍጠር ያልቻሉበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም ሌላ ሆነው የመጡት የካዎች በፈጣን የጨዋታ ሽግግር ተደጋጋሚ ማጥቃቶችን ያደረጉ ቢሆንም ከመከላከል ይልቅ ይበልጥ ማጥቃትን የመረጡት ሶዶ ከተማዎች ሁለተኛው የውሃ እረፍት ሊሰጥ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት በ70ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል ተቀይሮ በገባው በሚናስ ሀይሉ የተቀነሰች ኳስ በየካ ተከላካዮች ተነካክታ አደገኛ ቦታ ለይ ለነበረው ሌላኛው ተቀይሮ ለገባው በረከት ገብሬ ደርሳ ተጫዋቹም አክርሮ መቷት የላይኛውን የግብ አግዳሚ ነክታ ወደ ግብነት ተቀይራለች።


ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ማጥቃታቸውን ያጠናከሩት የካዎች በ79ኛ ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የቀኝ ጠርዝ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ካሳሁን ገ/ሚካኤል (ጎዶ) ወደ አደገኛ ቦታ አሻምቷት የቀድሞው የወላይታ ድቻ አማካይ እና የአሁኑ የሶዶ ከተማ አምበል አሸናፊ ሽብሩ በራሱ ግብ ላይ በግምባር አስቆጥሮ የካዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከአቻነቷ ግብ መቆጠር በኋላ ሁለቱም በድኖች የማሸነፍያ ጎል ለማግኘት እረፍት አልባ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ጨዋታው ጥሩ ፈክክር ታይቶበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ጥቂት ደቂቃዎችን እንደተጫወቱ የሶዶ ከተማው አማካይ እና በጨዋታው ልዩነት ለመፍጠር ሲዳዳ የነበረው ኃይለየሱስ ኃይሌ ከባድ ጉዳት አጋጥሞት ሲወድቅ የየካ የህክምና ባለሙያ አሸናፊ አምሳሉ ፈጥኖ በመግባት የመጀመርያ እርዳታ ከሰጠው በኋላ በጀርባው ተሸክሞ ተጫዋቹን ከሜዳ ያወጣበት ክስተት በተመልካቾች ዘንድ በአድናቆት እንዲያሰጠው ያደረገ ክስተትም ተከስቶ መመልከት ችለናል።

በዛሬው የዚህ ምድብ ጨዋታዎችን ለመከታተል የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኝ ከሆኑት መካከል የወልቂጤው ተመስገን ዳና እና የአርባምንጩ መሳይ ተፈሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በማሰብ በስታዲየሙ ታድመዋል፡፡