የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ 14ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ ሁለት የ14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ተደርገው የካ ክፍለከተማን እና ሀምበሪቾ ዱራሜን ባለ ድል አድርጓል፡፡

8፡00 ሲል ጅማ አባ ቡናን ከ የካ ክፍለከተማ ያገናኘው መርሃግብር የዕለቱ ቀዳሚው ጨዋታ በየካ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጅማዎች በጥሩ የኳስ ቅብብሎች ጀምረው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ቀስ በቀስ የጅማን የመከላከል አደረጃጀት በመስበር በመልሶ ማጥቃት የካ ክፍለከተማዎች ጥሩ ሲጫወቱም ታይቷል፡፡ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ከተጋጣሚያቸው ሻል ብለው የታዩት ጅማዎች በ13ኛ ደቂቃ ላይ የቀድሞው የጅማ አባጅፋር አጥቂ ብዙአየሁ እንደሻው ከቀኝ መስመር በኩል በረጅሙ ያሻማውን ኳስ የግራ መስመር አጥቂው ኑርላይን አብዱሰመድ ሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ ከተቆጣጠረው በኋላ የግብ ጠባቂውን የአቋቋም ስህተት ተጠቅሞ ግሩም ጎል ለአባቡናዎች አስቆጥሯል፡፡

በዚህኛው አጋማሽ ጅማዎች ብዙ የማስቆጠር አቅም ያላቸው ቢመስልም እጅግ ደክሞ የታየው የመጠቀም ክፍተታቸው በሂደት ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስላል፡፡ በአንፃሩ የአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው ቡድን የካ አቻ ለመሆን ቢታትሩም ወደ ሶስተኛው የማጥቂያ ክፍል ሲደርሱ መዳከሞች በደንብ ታይቶባቸዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ጅማ አባጅፋር በረጃጅም ኳስ የካዎች በተጠና የጨዋታ ሂደት ሁለት ጎል አግኝተዋል፡፡ 88ኛው ደቂቃ መሀሪ ዮሴፍ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አላዛር ዝናቡ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑ ወደ አቻነት ሲያሸጋግር በጭማሪ ደቂቃ ደግሞ በጅማ የሜዳ ክፍል ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ካሳሁን ገብረሚካኤል በፍጥነት በማስጀመር ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው መስፍን ዳንኤል ሰጥቶት ተጨዋቹ ወደ ጎልነት በመለወጥ የካን 2ለ1 አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡

የሳምንቱ የመጨረሻ እና ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የ10፡00 ጨዋታ በሀምበሪቾ ዱራሜ እና ጉለሌ ክፍለከተማ መካከል ተከናውኗል፡፡ የመሀል ሜዳ አስደናቂ ፉክክር የታየበት እና በአንፃራዊነት የሀምበሪቾ ዱራሜ ቶሎ ቶሎ የማጥቃት የበላይነት በመጀመርያ አጋማሽ ላይ የታየ ቢሆንም ወደ ፊት ሄዶ ጎልን ከመረብ ማዋሀዱ ላይ ደካማ በመሆናቸው ግብ መመልከት ሳንችል ቀርተናል፡፡

ከእረፍት መልስ ሙሉ በሙሉ የተዋሀደ የጨዋታ ቅርፅን ያሳዩት የአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞው ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በ59ኛ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የቀድሞው የደደቢት ተጫዋች ዳግማዊ አባይ ያሳለፈለትን ኳስ ከደሴ ከተማ ዘንድሮ ቡድኑን መቀላቀል የቻለው አማካዩ ልዑልሰገድ አስፋው በጥሩ ሁኔታ ከተቆጣጠረው በኋላ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ ሀምበሪቾዎችን 1ለ0 አሸናፊ አድርጓል፡፡