የሊጉ የዓምና እና ዘንድሮ የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች ንፅፅር (ክፍል 2)

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በክፍል አንድ ጥንክራችን ከዓምና ዘንድሮ የውጤት መንሸራተት ያጋጠማቸው ክለቦች ቁጥሮችን መነሻ በማድረግ በስፋት የተመለከትን ሲሆን አሁን ደግሞ በተቃራኒው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦችን ለመቃኘት እንሞክራለን።

ሊጉን ዘንድሮ ከተቀላቀሉ ሦስት ክለቦች ውጪ ከፍተኛ የውጤት መሻሻል ያስመዘገበው ክለብ አዳማ ከተማ ነው። ዓምና በ15 ጨዋታዎች 7 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ 12 ጨዋታዎችን ተሸንፎ 30 ግቦችን በማስተናገድ በ18 የግብ ዕዳ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ የነበረው ክለቡ ዘንድሮ በ14 ነጥቦች ልቆ 21 ነጥቦችን በመያዝ በሊጉ ሁለተኛው ዝቅተኛ ጨዋታዎችን የተሸነፈ ቡድን በመሆን (ከሲዳማ ቡና ጋር ዕኩል 2) ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ዓምና በአሠልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል እና ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ 15ቱን ጨዋታዎች ያከናወነው አዳማ ዋነኛ ችግሩ ግቦችን ማስተናገድ ነበር። ከ15ቱ ጨዋታዎችም አንዱ ላይ ብቻ ነበር ግብ ሳያስተናግድ ወጥቶ የነበረው። በዚህም የሊጉ ከፍተኛ ግቦችን ያስተናገደ ቡድን ሆኖ ነበር። የዘንድሮ አዳማ ከተማ ግን ከዓምናው በተለየ ግቡ በቀላሉ የማይገኝ ሆኖ ቀርቧል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠልም ሁለተኛው ጥቂት ግብ ያስተናገደ ክለብ መሆን ችሏል። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዴም ቢሆን ለተጋጣሚ ከአንድ በላይ ግብ እንዲያስቆጥር ፈቅዶ አያውቅም። ይህ የመከላከል ጥንካሬ ከወገብ በላይ አለመደገፉ ነው እንጂ አዳማ አሁን ካለበት ደረጃ ተመንድጎ በተቀመጠ ነበር።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በሚገባ ራሱን ማጠናከሩ ከዓምናው ስህተቱ እንደተማረ የሚጠቁም ነው። በድምሩ 13 ተጫዋቾችን አስፈርሞ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ክለቡ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የነበረውን የተጫዋች ጥራት ችግር ለማሻሻል ሞክሯል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃም ከአሠልጣኝ ጀምሮ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት የቡድን ግንባታውን ከመከላከል በመጀመሩ ከላይ እንደገለፅነው ዋጋ አግኝቷል።

እንደጠቀስነው በማጥቃቱ ረገድ ግን መጥፎ የውድድር ዓመት ካሳለፈበት የ2013 የመጀመሪያ 15 ጨዋታዎች እንኳን የተሻለ ግብ ማግኘት አልቻለም። በዚህም ዓምናም 12 ዘንድሮም 12 ግቦችን ነው ያስቆጠረው። ይህ ብቻ ሳይሆን ዓምና በአንድ ጨዋታ አራት ግብ ፣ በሌላ ጨዋታ ሦስት ግብ እንዲሁም ተመሳሳይ በሌላ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ ሲታወስ እና ዘንድሮ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ሦስት በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ብቻ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሩ (አንዱም በፍፁም ቅጣት ምት የተገኘ ነው) ሲታይ ተሻሽሏል ያልነው ቡድን ከፊት የስልነት ችግር እንዳለበት ያመላክታል።

በአዳማ መሻሻል ውስጥ ያለ ሌላኛው የሚያሳማ ጉዳይ የአቻ ውጤቶች መብዛታቸው ነው። ቡድኑ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 60% የሚሆነውን ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ከምንም አንድ ይሻላል የሚባለው ብሂል እንዳለ ሆኖ ቡድኑ አቻ ከወጣቸው 9 ጨዋታዎች በ4ቱ እየተመራ የነበረ መሆኑ እንዲሁም ድል ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአንዱ (ሰበታ ከተማ) በተመሳሳይ እየተመራ መሆኑ የአቻ ውጤቱ ጥሩ እንደሆነ ቢያሳይም ቀድሞ ግብ እያስተናገደ ዳግም አቻ ለመሆን መሯሯጡ ግን ዋጋ ያስከፈለው ዋነኛ ነገር እንደሆነ ይታመናል። በተለይ ቀድሞ ግብ ያስቆጠረው ክለብ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት የሚያደርገውን የመከላለል ጥረት ሰብሮ ለመግባትም ይቸግራል።

ከአዳማ በመቀጠል ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው ክለብ ሲዳማ ቡና ነው። ዓምና በመጀመሪያዎቹ 15 ጨዋታዎች 14 ነጥቦችን ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ከፍ ብሎ የነበረው ሲዳማ ዘንድሮ ከወራጅ ቀጠናው በ11 ነጥቦች እና 9 ደረጃዎች ርቆ 5ኛ ደረጃን ተቆናጧል። በሁለት ጊዜ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ዘንድሮ ከዓምናው የከፋ አጀማመር ቢያደርግም ቀስ በቀስ ለውጥ በማሳየት ደረጃውን አሻሽሏል። ዓምናው በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደገባ ሲታመን የነበረው ክለብ በመጀመሪያዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ሦስት ድሎችን ሲያገኝ ዘንድሮ ግን አንዱን ብቻ ነበር ያሸነፈው። ልዩነቱ ዘርዓይ የመሩት ቡድን ከ10 ጨዋታዎች ግማሹን የተሸነፈ ሲሆን የዘንድሮ የገብረመድህን ስብስብ ግን ከ10ሩ ሁለቱን ብቻ ነው የተረታው።

በአብዛኛው በ4-3-1-2 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ የሚጫወተው ሲዳማ የቡድኖች አከርካሪ (Spine) ተደርጎ በሚወሰደው ቦታ ግንባታውን እንዳደረገ ይታመናል። በዚህም መሐል ለመሐል ከግብ ጠባቂው እስከ መጨረሻ አጥቂው የሚሰለፉት ተክለማርያም፣ ያኩቡ፣ ፍሬው እና ይገዙ 15ቱም ጨዋታዎች ላይ የተሳተፉ ብቸኞቹ ተጫዋቾች ናቸው። እነዚህን ተጫዋቾች መነሻ በማድረግ በሚከናወኑት አምስቱም የጨዋታ ምዕራፎች (መከላከል፣ ማጥቃት፣ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር፣ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር እና የቆመ ኳስ አጠቃቀም) ላይም ከዓምናው በተሻለ ዕድገት አሳይቷል። በዋናነት ደግሞ በቡድናዊ መዋቅር ከኳስ ውጪ መታተር እና ሽግግሮችን በአግባቡ መጠቀም ከዓምናው የተሻለበት ጉዳይ ነው። ከምንም በላይ ግቦችን የማስተናገድ አባዜ ተጠናውቶት የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ መሠረቱን በተሻለ መዋቅር ገንብቶ መምጣቱ ለለውጡ ዋነኛ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። ለማሳያ ዓምና 22 ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን ዘንድሮ ግን በ10 ቀንሶ 12 ጎሎችን ብቻ ለተጋጣሚ ሰጥቷል።

ከወገብ በላይ ስልነት ጨምሮ የመጣው ሲዳማ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ በሚገኘው ይገዙ ቦጋለ ብቃት እጅጉን እየተጠቀመ ይገኛል። ዓምና በ15ቱ ጨዋታዎች ምንም ጎል አስቆጥሮ በማያውቀው እና በ21 የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጎል ያገኘው ይገዙ ዘንድሮ የቡድኑን ለግማሽ የተጠጋ ኳስ ከመረብ አዋህዷል። እሱ ብቻ ሳይሆን ዓምና በ15ቱ ጨዋታዎች 2 ግብ ብቻ አስቆጥሮ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝም ዘንድሮ እጥፍ ጎል በስሙ አስመዝግቧል። የሁለቱ አጥቂዎች ምርጥ ብቃት ላይ መገኘት ያለ ጥርጥር ጠቃሚ ቢሆንም ቡድኑ ከእነርሱ ውጪ በክፍት ጨዋታ ኳሶችን የሚያስቆጥርለት እና ጫናዎችን የሚጋራ ተጫዋች የሚፈልግ ይመስላል። በተመሳሳይ የጨዋታ ቁጥር ዓምና 5 ተጫዋቾች በክለቡ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የነበሩ መሆኑ እና ዘንድሮ ስድስት መኖራቸው በግብ ስብጥሩ ረገድ መጠነኛ ዕድገት እንዳለ ቢያሳይም ከይገዙ እና ሀብታሙ 12 ጎሎች ውጪ ከተቆጠሩት አምስት ጎሎች አንዱ ብቻ በክፍት ጨዋታ መሆኑ ጉዳዩን የጎላ ያደርገዋል። በዚህም ፍሬው ሰለሞን ድሬዳዋ ላይ ካስቆጠራት የ75ኛ ደቂቃ ጎል ውጪ ዳዊት ተፈራ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን እንዲሁም ግርማ በቀለ እና ብሩክ ሙሉጌታ ከመዓዘን ምት መነሻን ካደረሱ ኳሶች ያስቆጠሩት ነው። በአጠቃላይ ሲዳማ ግቦችን በማስቆጠር ቢሻሻልም የግብ ምንጮችን በማስፋቱ ረገድ ግን ክፍተት አለበት።

በቡድኑ ዕድገት መጠቀስ ያለባቸው ዋነኛው ሰው ደግሞ አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ናቸው። አሠልጣኙ አሁን ብቻ ሳይሆን ዓምናም ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ያሳዩት ለውጥ የማይዘነጋ ሲሆን ዘንድሮም የራሳቸውን የተጫዋቾች ምርጫ በማድረግ ሙሉ የቅድመ ውድድር ዝግጅት አከናውነው ያሳዩት ብቃት ከዓምናው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ነው። በዋናነት ጨዋታን የማንበብ እና የመለወጥ አንፃራዊ ብቃት ይነሳል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ እየተመራ የጨዋታውን ውጤት ለመገልበጥ እና ለማሸነፍ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ብዙ ጊዜ የተዋጣላቸው ነበሩ። ባህር ዳር እና ሀዲያን ያሸነፉበት መንገድም ለዚህ ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተጫዋቾቻቸው ላይ ያላቸው ትዕግስት እና ዕምነት ዋጋ ከፍሏቸዋል። ለምሳሌ ሀብታሙ ፣ ይገዙ እና ዳዊትን በሚገርም ትዕግስት ወደ