የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የ15 ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ወደ መጠናቀቂያው እየተቃረበ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር 15ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር በምድብ ሀ በሰንጠረዥ አናት የሚገኙ ቡድኖች ጨዋታቸውን አድርገዋል። ኤሌከትሪክ መሪነቱን ያሰፋበትን ፣ ባንክ ይበልጥ ወደ አናት የተጠጋበትን ድል ሲያስመዘግቡ ነጌሌ አርሲ ሽንፈት አስተናግዷል።

ረፋድ ላይ ሸሸመኔ ከተማን የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ ከቀረበው ሻሸመኔ ጠንካራ ፉክክር የገጠመው ኤሌክትሪክ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ይፈፅማል ተብሎ ሲጠበው በጭማሪ ደቂቃ ላይ ምንያህል ተሾመ ወሳኟን ግብ አስቆጥሮ ማሸነፍ ችለዋል። ይህ ውጤትም ኤሌክትሪክ ከተከታዮቹ በ4 ነጥቦች ርቆ በ32 ነጥቦች መሪነቱን እንዲያጠናክር ረድቶታል።

ስምንት ሰኣት ላይ በሁለተኛ ዙር ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታይ ደረጃ ላእ የተቀመጠው ጋሞ ጨንቻን ገጥሞ 2-1 ማሸነፍ ችሏል።  የኋላሸት ሰለሞን ባንክን በ10ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ያደረገ ቢሆንም ማቲዮስ ኤልያስ በ14ኛው ደቂቃ ጨንቻን አቻ አድርጎ ነበር። ሆኖም በድጋሚ የኋላሸት ሰለሞን በ17ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ሃምራዊዎቹን ባለ ድል አድርጓል። ይህ ውጤትም ባንክ ነጥቡን 28 አድርሶ ሁለተኛ ደረጃ ከተቀመጠው ነጌሌ አርሲ ጋር እንዲስተካከል አድርጎታል።

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነጌሌ አርሲ በባቱ ከተማ የ1-0 ሽንፈት አስተናግዷል። ሳላሃዲን ሙሰማ በ50ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ባቱ ከተማን ሦስት ነጥብ ማስጨበጥ ችላለች። ውጤቱን ተከትሎ ከአንደኛው ዙር አስደናቀ ጉዞው እየተቀዛቀዘ የሚገኘው ነጌሌ አርሲ ከመሪው ያለው ርቀት ወደ አራት ሰፍቷል።