ጦሩ አራተኛ ተጫዋቹን ከእንግሊዝ በማምጣት አስፈርሟል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው መከላከያ በ8 ዓመቱ ከኢትዮጵያ የወጣውን ተጫዋች የግሉ አድርጓል።

በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ በ15 ሳምንታት የሊጉ ጨዋታዎች 18 ነጥቦችን ሰብስቦ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ የሚታወቅ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ ከቀናት በፊት በተከፈተው የዝውውር መስኮት በስፋት እየተሳተፈ ይገኛል። በተከታታይ አሚኑ ነስሩ፣ እስራኤል እሸቱ እና ምንተስኖት አዳነን የግሉ ያደረገው ክለቡ ዛሬ ደግሞ የመስመር ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ክለቡን በአንድ ዓመት ውል የተቀላቀለው ተጫዋች አሚን መሐመድ ይባላል። በአፋር የተወለደው አሚን ገና በስምንት ዓመቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሄድ እድገቱን ያደረገ ሲሆን በተለያዩ የሊግ እርከን በሚገኙ የዌልስ እና እንግሊዝ ክለቦች በሙሉ እና በከፊል ፕሮፌሽናልነት ተጫውቶ አሳልፏል። በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የመጨረሻ ወራት በሰሜን ዌልስ ለሚገኘው ባክሊይ የተጫወተ ሲሆን ከክለቡ ጋር ተለያይቶም ወደ ትውልድ ሀገሩ በመመለስ ያለፉትን ቀናት በመከላከያ የሙከራ ጊዜ ተሰጥቶት ነበር። ሙከራውን በማለፍም ለክለቡ ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።