ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጓል

2010 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የተሰናበቱት ቀይ ለባሾቹ ጌዲዮ ዲላን መርታታቸውን ተከትሎ ለከርሞው ወደ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መመለሳቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ ከተዋቀረበት ከ1990 ጀምሮ
ሁለት ጊዜ የቻምፒዮንነት ታሪክ የነበረው እና በወጣቶች የተገነቡ ቡድኖችን በመጠቀም ስሙ በበጎ ይነሳ የነበረው ኢትዮ ኤሌክተሪክ የተፎካካሪነት ደረጃው ቀስ በቀስ እየወረደ እና የወራጅ ቀጣናው ደንበኛ እየሆነ መጥቶ በመጨረሻም ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዷል። 2010 ላይ ሊጉን ከመሰናበቱ ቀደም ብሎም በተደጋጋሚ ይህ አደጋ ይጋረጥበት የነበረ መሆኑ መውረዱን ተከትሎ የክለቡ ህልውና ያበቃል የሚል ስጋትም ተፈጥሮ ነበር።

ሆኖም ክለቡ እስትንፋሱ ቀጥሎ በከፍተኛ ሊጉ በ2011 እና በ2013 ዳግም ለመመለስ ጥረት ቢደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። በተለይም ባሳለፍነው ክረምት የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት ሀዋሳ ላይ በተደረገው ውድድር የፕሪምየር ሊግ ትኬቱን ይቆርጣል ተብሎ ቢጠበቅም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ዘንድሮ በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እየተካሄደ በሚገኘው የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ውስጥ የተደለደለው ክለቡ በጠንካራ ፉክክር ውስጥ ቆይቶ ከነገሌ አርሲ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአንደኝነት ለመጨረስ ሲፋለም ቆይቷል። ዛሬ ረፋድ ባህር ዳር ላይ በተደረገ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጌዲዮ ዲላን 2-0 መርታቱን ተከትሎ አንድ ጨዋታ እየቀረው ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ መግባቱን አረጋግጧል።

በሌላ የምድቡ ጨዋታ ተከታዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገላን ከተማ ጋር ነጥብ በመጋራቱ ዳግም በተቋቋመበት ዓመት ወደ ሊጉ የመመልስ ህልሙ ከሽፏል።