የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-2 ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ሁለተኛውን ዙር በድል በከፈተበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

“ጨዋታውን ባሰብነው መልኩ ለማስኬድ ሞክረናል ነገርግን ራሳችን በሰራናቸው ስህተቶች ዋጋ ከፍለናል ፤ ስለዚህ እንቀበላለን።

በጨዋታው ድክመት ስለነበረበት የሜዳ ክፍል

“ያገኘናቸውን ዕድሎች በአግባቡ አልተጠቀምንም ይህም ዋጋ አስከፍሎናል ፤ ነገርግን የኳስ ሂደቱ ጥሩ ነገር አለው።

በዛሬው ጨዋታ ስለተማሩት

“እግርኳስ የስህተት ስፖርት ነው ፤ ስህተቶቻችንን አርመን መቅረብ የውዴታ ግዴታችን ነው።

ከሜዳ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ተፅዕኖ

“በልጆቹ ላይ ጥሩ ሆነው መቅረባቸው ለራሳቸውም ሆነ ለክለቡ ጠቃሚ ስለመሆኑ በደንብ ተነጋግረናል። በዚህም ልጆቹ የተቻላቸውን ሜዳ ላይ ሰጥተዋል ፤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ወደፊትም የተሻለ ነገር እንደሚሰሩ አምናለሁ።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“መሀል ላይ ብልጫ ወስደው ይጫወቱ ነበር። እኛም በ3-5-2 በመግባት ያንን እንዳይወስዱ ለማድረግ ሞክረናል። ግን ዞሮ ዞሮ ለ20/25 ደቂቃ ጫናችን ትክክል ስላልነበር ብልጫ ተወስዶብናል። በሁለተኛው አጋማሽን ያንን በማስተካከል ብዙ አጋጣሚዎችን ፈጥረናል ግን መጀመሪያ ላይ በተወሰነ መልኩ ተበልጠናል።

ዕድሎችን ስላለመጠቀም

“የእነሱ ግብ ጠባቂ እኛ ጋር የነበረ ስለነበር ከልጆቹ ጋር ይተዋወቃል ፤ በዚህም ብዙ ኳስ አድኖብናል። የእኛም ልጆች የአጨራረስ ችግር ነበረብን። ዞሮ ዞሮ ለቀጣይ ጠንክረን መስራት አለብን ምከንያቱም ከሌላ ቡድን ጋር እንደዚህ ዕድል ላታገኝ ትችላለህ። በመሆኑም ዕድል ፈጥረህ መጠቀም ካልቻልክ ትርጉም ስለማይኖረም በደንብ ማሻሻል ይኖርብናል።”