ፈረሰኞቹ ወሳኝ አጥቂያቸውን መቼ ያገኛሉ ?

የሊጉን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኛው የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ መቼ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ አጣርተናል።

ዘንድሮ የውድድር ዘመን ፈረሰኞቹ ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ቶጎዋዊ አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ሊጉ ከአንደኛው ዙር መጠናቀቅ በኋላ ሲጀምር ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግልጋሎት እየሰጠ አይገኝም።

ሶከር ኢትዮጵያም ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ከጨዋታ የራቀበትን ሁኔታ ለማወቅ ባደረገችው ማጣራት በጉዳት ምክንያት ክለቡ እንደማይገኝ እና ሀገሩ እንዳለ አረጋግጣለች። አሁን የጤንነት ሁኔታው መሻሻል እያሳየ መሆኑን ተከትሎ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ሲሆን በ18ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬደዋ ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የማይደርስ ቢሆንም በቀጣይ ፈረሰኞቹ ከመከላከያ በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ክለቡ የቶጎዊውን አጥቂ ግልጋሎት እንደሚያገኝ ሰምተናል።

ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ እስከ አስራ ሰባተኛ ሳምንት በዘለቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስር ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ መሆኑ ይታወቃል።