ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

በጨዋታ ሳምንቱ ጅማሮ አንጋፋዎቹን የሚያገናኘውን ግጥሚያ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በሊጉ አናት ተቀምጦ ግስጋሴውን ቀጥሏል። አራት ተካታታይ ጨዋታዎችን ድል ያደረገው ቡድኑ ከአርባምንጭ እና ሀዲያ ሆሳዕና የአቻ ውጤቶች በኋላ ነጥብ የከለከለው ክለብ አልተገኘም። የነገው የጊዮርጊስ ተጋጣሚ ሌላኛው ዕድሜ ጠገብ የሊጉ ክለብ መከላከያ ምንም እንኳን ጥሩ አቋም ላይ ባይሆንም ወትሮም ሁለቱ ሲገናኙ የሚታየው ጥሩ ፉክክር ከጨዋታው ይጠበቃል። ያም ሆኖ ጦሩ ከታሪክ ውጪ በጨዋታው ላይ የሚኖረውን የፉክክር ደረጃ ወቅታዊ አቋሙ የሚያጠናክርለት አይደለም። በዚህም ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳካው ቡድን ለወራጅ ቀጠናው በደረጃም በነጥብም መቅረቡ የነገውን ውጤት ከተጋጣሚው በላይ እንዲፈልገው ያደርገዋል።

ከውጤት ባለፈም ነገሮች በሁሉም መልኩ ለሊጉ መሪዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱላቸው ነው። ዋና ግብ አስቆጣሪያቸው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ባይኖር በተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ እና ሌሎች አጥቂዎቻቸው ግቦችን እያገኙ ሲቀጥሉ እስካሁን ሽንፈት ባላስተናገደው ቡድን የኋላ መስመር በኩልም በመጨረሻዎቹ 12 ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ማስተናገዳቸው ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስረዳ ነው። ለቀጥተኝነት ያመዛነው የዘንድሮው ጊዮርጊስ በፈጣን ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን በቆሙ ኳሶችም ግቦችን በማግኘት ላይ ነው። በዚህ መልኩ በብዙ አቅጣጫዎች የተሳለ መሆኑ ጨዋታዎችን ከፍ ባለ ጉልበት ከሚጀምርበት አግባብ ጋር ተደምሮ ኳስ ተቆጣጥረው ለሚጫወቱ እንደመጨረሻ ተጋጣሚዎቹ ሰበታ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ላሉ ቡድኖች ይበልጥ ከባድ አድርጎታል። ሆኖም ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ከመጨረሻ ተጋጣሚዎቹ የተለየ ባህሪ ያለው ቡድን እንደሚጠብቀው መረዳት እንችላለን።

መከላከያ ባለፉት ጨዋታዎች ከሌላው ጊዜም በባሰ ሁኔታ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ ቀንሶ ታይቷል። በዚህ ላይ ዋና መሪው አሌክስ ተሰማን ያጣው የቀደመ የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆነው የተከላካይ መስመሩም ግቦች ማስተናገድ መጀመሩ ከውጤት አርቆት ቆይቷል። በአዲስ አበባው ጨዋታ ቡድኑ ከ 4-4-2 ወደ 4-2-3-1 በመመለስ ለዋነኛው የፈጠራ ምንጩ ቢኒያም በላይ የአስር ቁጥር ሚና ሰጥቶ ታይቷል። ቡድኑ ወደዚህ ቅርፅ ከቆይታ በኋላ እንደመመለሱ ኳስ በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ እምርታን ቢያሳይም አሁንም በበቂ ሁኔታ ዕድሎችን ሳይፈጥር ሽንፈት አስተናግዷል። የመጨረሻው ጨዋታ ከሄደበት አግባብ እና ከነገ ተጋጣሚው ክብደት አንፃርም ቡድኑ በጨዋታ ዕቅድ ደረጃ ወደ ጥንቃቄ አቀራረቡ እንዲሁም ከአሰላለፍም ደረጃ በተመሳሳይ የመስመርም ሆነ መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በሁለት ረድፍ መከላከል ወደሚያስችለው 4-4-2 ሊመለስ አልያም በ3-5-2 ሊገባ ይችላል።

መከላከያ አሁን ላይ ጊዮርጊስን እንደፈተኑት አርባምንጭ እና ሆሳዕና በሙሉ ጨዋታው በትኩረት የመከላከል አቅሙ አብሮት ነው ማለት ይከብዳል። በተመሳሳይ ከተከላካይ መስመር ጀርባ ሰፊ ክፍተት ላያገኝ የሚችለው ቅዱስ ጊዮርጊስም ነገሮች ቀላል ላይሆኑለት ይችላሉ። በዚህም ፈረሰኞቹ ጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙት የማጦቃት ባህሪ ካላቸው አማካዮቻቸው ተጨማሪ ጥረት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

በመከላከያ በኩል ለመልሶ ማጥቃት ምቹ የሚመስለው አዲሱ አጥቂ ባዳራ ናቢ ሲላን ያነጣጠሩ ኳሶችን ከፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጋር መፍጠር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የጊዮርጊሶች የማጥቃት ቅብብሎች በቀድሞው ተጫዋቻቸው ምንተስኖት አዳነ እና ኢማኑኤል ላሪያ በመሀል እንዲሁም ብዙም ረቀው በማይሄዱት የመስመር ተከላካዮች ሊደፍኑ የሚችሉትን የጦሩ ኮሪደሮች የማስከፈት የቤት ስራ ይጠበቃል። ጦሩም ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ራሱ የሜዳ ክፍል መሳብ እና ኳሶችን አቋርጦ በፍጥነት ከሜዳው ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት በፍጥነት የመከላከል ሽግግሩን ከሚቀላቀሉት ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ያለው የሚጠብቀው ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የተለየ የጉዳትም የቅጣትም ዜና ባይኖርም ለነገው ጨዋታ የማይደርሰው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ እንደሚገባ ተሰምቷል። ከዚህ በተጨማሪ ቡልቻ ሹራ ወደ ሙሉ ልምምድ ተመልሶ ነገ ከቡድኑ ስብስብ ውስጥ እንደሚቀላቀል ታውቋል። በመከላከያ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት የብሽሽት ጉዳት የገጠመው ሠመረ ሀፍተይ እና አሌክስ ተሰማ አለማገገማቸው ታውቋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ አንጋፋ ክለቦች በሊጉ 29 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ 12 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን በረጅም ርቀት ሲይዝ መከላከያ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶያል ፤ ቀሪ 15 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። ቅዱስ ጊዮርጊስ 35 መከላከያ ደግሞ 16 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱለይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – ያብስራ ተስፋዬ – ቸርነት ጉግሳ

አማኑኤል ገብረሚካኤል

መከላከያ (4-4-2)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ

ግሩም ሀጎስ – ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ – ቢኒያም በላይ

ተሾመ በላቸው – ባዳራ ናቢ ሲላ