ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የ19ኛ ሳምንት የመክፈቻ ቀን ሁለተኛ መርሐ-ግብር ላይ ያተኮረው ዳሰሳችን እንዲህ ይቀርባል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ ለማፋጠን እና ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት የሁለት ለምንም ሽንፈት ለማገገም ድልን እያለመ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲታሰብ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አሁንም የሚገኘው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ያለ መሸነፍ ግስጋሴውን ወደ 12 ለማሳደግ እና በቀጣዩ ሳምንት ከሊጉ መሪ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ጥሩ ስንቅ ለመያዝ ጠንክሮ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይገመታል።

በ18ቱ የሊጉ ጨዋታዎች ጥቂት (2) ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚው የሆነው ሰበታ ከተማ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ እንደታመመ ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከወገብ በላይ መጠነኛ ለውጦችን አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቶ የነበረው ቡድኑም አንፃራዊ መሻሻል በተጋጣሚ ሜዳ ቢያስመለክትም በሁለተኛው አጋማሽ ግን እንደ ቀደመው ተቀዛቅዞ ነበር። በተለይ አሠልጣኝ ብርሃን ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አብዱልሀፊዝ እና ፍፁምን ከቀየሩ በኋላ የቡድኑ የፈጠራ አቅም ትንሽ ተዳክሞ ታይቷል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ቢበለጥም በአጠቃላይ በድምሩ 19 የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ የኢትዮጵያ ቡናን መረብ ለማግኘት ጥሮ ነበር። የግብ ዘቡ በረከት አማረ አልቀመስ ማለቱ ውጥናቸውን አላሳከ አላቸው እንጂ ከወትሮ በተለየ በተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ እየተገኙ ነበር።

ባለፉት 10 ጨዋታዎች 21 ግቦችን ያስተናገደው ሰበታ አሁንም የኋላ መስመሩን በሚገባ ማጠናከር የግድ ይለዋል። የበረከት እና አንተነህ ጥምረት መጥፎ ባይሆንም ተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ ሲጋለጡ ይስተዋላል። የነገው ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና ደግሞ ከአጥቂዎቹ በተጨማሪ ከአማካይ እየተነሱ ሳጥን የሚገቡ እንዲሁም የመጨረሻ ኳሶችን የሚያመቻቹ አማካዮች ስላሉ የበለጠ እንዳይቸገር ያሰጋል። ይህንን ተከትሎም ምናልባት ኳሱን ለሲዳማ ተጫዋቾች ትተው በቁጥር በርከት ብለው ክፍተታቸውን ለመሸሸግ ሊጥሩ እንደሚችሉ ይታሰባል። በዚህ ሂደት ፈጣን የመልሶ ማጥቃቶችን በመሰንዘር ግብ ለማግኘት እንደሚጥሩም ይገመታል።

የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስብስብ ባሳለፍነው ሳምንት ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ሀዋሳ ከተማን 3ለ1 ረቶ ለነገው ጨዋታ መቅረቡ ትልቅ የራስ መተማመን እንደሚሰጠው መናገር ይቻላል። በጨዋታው ቡድኑ ድል ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት፣ በቆሙ ኳሶች እንዲሁም በሽግግሮች የነበረው ብቃት ምርጥ ነበር። በተለይ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው የተጫወቱበት መንገድ ድንቅ ነበር። በነገው ፍልሚያ ግን ሰበታ ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ፍላጎት ላያሳይ ስለሚችል ከኳስ ጋር የሚያሳልፉበት ጊዜ ሊረዝም ይችላል። በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ብቃት ከሚሰጡ እና ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፈው ከነበረው 4 ተጫዋቾች መካከል ፍሬው ሰለሞን በቅጣት ምክንያት አለመኖሩ መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶችን ሊያቀዘቅዝ እንደሚችል ቀድሞ መገመት ቀላል ነው። ሰበታዎችም ይህን እንደ ጥሩ ዜና ሊወስሱት የሚችሉት ጉዳይ ነው።

ሽንፈት ከገጠመው 11 ጨዋታዎች ያለፉት ሲዳማ ቡና በነገው ጨዋታ በመስመር በኩል በማጥቃት ጨዋታውን ለመወሰን እንደሚጥር ይገመታል። በማጥቃት ላይ በመሳተፍ ጥሩ የሆኑት የመስመር ተከላካዮችም ዋነኛ አማራጮቹ እንደሚሆኑ እሙን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ከመስመር እየተነሳ እንዲያጠቃ ሀላፊነት የተሰጠው ይገዙ የሚያደርጋቸው ሩጫዎችም ለሰበታዎች አደገኛ ናቸው። ስለ ሲዳማ ሲነሳ ግን ስለ መሐል ተከላካዮቹ ብቃት ሳያነሱ ማለፍ እጅግ ከባድ ነው። የጊት እና ያኩቡ ጠንካራ የኋላ መስመር ጥምረት ደግሞ ድክመት ላለበት የሰበታ የፊት መስመር ብዙ ስራን የሚያበዛ ነው።

ሰበታ ከተማ አንተነህ ናደውን በህመም ጌቱ ኃይለማሪያምን ደግሞ በአምት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኝም። ሲዳማ ቡናም የአምበሉ ፍሬው ሰለሞንን ግልጋሎት በቅጣት ምክንያት አያገኝም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሲዳማ ቡና 4 ሰበታ ከተማ ደግሞ 1 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ


ሰበታ ከተማ (4-4-2)

ምንተስኖት አሎ

ታፈሰ ሰርካ – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ሳሙኤል ሳሊሶ – በኃይሉ ግርማ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ፍፁም ገብረማርያም – ዴሪክ ኒስባምቢ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

ደግፌ ዓለሙ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ይገዙ ቦጋለ – ሳልዓዲን ሰዒድ – ሀብታሙ ገዛኸኝ