የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 0-3 ሲዳማ ቡና

ሳላዲን ሰዒድ ሐት-ትሪክ ከሰራበት የምሽቱ የሰበታ እና ሲዳማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው እንደጠበኩት አይደለም በብዙ መልኩ ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው፡፡ ለማሸነፍ ነበር የመጣነው እና በመጀመሪያ ደቂቃ ላይ የገባብን ጎል ተጫዋቾቼ ላይ የመውረድ ነገር መጥቷል። እንደገና ሁለተኛ ጎል ሲደገም ሁለት ለባዶ ዕረፍት ስንሆን የበለጠ መውረድ መጥቷል። ለመነሳት ብዙ ጥረት አደረግን ብዙ ተመካከርን እንደውም ሁለተኛውን አርባ አምስት የበለጠ ለማጥቃት እንሞክራለን ነበር ያልነው ሳይሳካልን ቀረ፡፡ በእኛ ተከላካዮች ስህተት ለመሸነፍ በቅተናል ፤ በጨዋታ ስህተት፡፡

ስለቡድኑ የአጨራረስ ችግር

“በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች በተለያየ ልምምድ ላይ የአጨራረስ ስራዎችን እንሰራለን። ኳስ የመጨረስ ስራዎችን እንሰራለን። ነገር ግን ጨዋታ ላይ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን አርሞ መግባት ሲጠበቅ የመሳት ነገሩ እንዳለ ሆኗል። ለዚህም እንፈጥራለን ጎል ለማግባት ብዙ ጥረቶችን እናደርጋለን። እንደርሳለን ግን ኳስን ከመረብ ለማገናኘት ችግሮች እየበዙብን መጥተዋል እና ለማስተካከል እንሞክራለን፡፡

ምክትል አሰልጣኝ አለመኖሩ የሀሳብ ዕጥረት ስለመፍጠሩ

“በእርግጥ አንድ ሰው ብቻውን በእግር ኳስ ላይ ምንም ሊያመጣ አይችልም፡፡ በጣም ብዙ የስታፍ አባሎች ሊኖሩህ ይገባል። እና ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አቅርቢያለሁ ሊቀርብልኝ አልቻለም፡፡ ያው ብቻዬን እየለፋው ነው ፤ የተቻለኝን ጥረት አደርጋለሁ፡፡ የሚመጣውን መቀበል ብቻ ነው፡፡”

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለተጋጣሚ ቅለት

“የጎሉን መብዛት አይደለም ትልቁ ቁም ነገር ጠንካራ ነበሩ። በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ምንም እንኳን ጎል ብናገባባቸውም ጥንካሬ ነበራቸው፡፡ በተለይ መሀሉ ላይ ተቆጣጥረው እየተጫወቱ ነበር፡፡ ሁለተኛው አርባ አምስት ደቂቃ ላይ ያንን ድልድያችን ተሰብሮ ስለነበር እሱን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል፡፡ ለመቆጣጠር ሞከርን በዚህ አጋጣሚ ሦስተኛ ጎል አገባን ትንሽ ጨዋታውን የገደልነው ይመስለኛል እንጂ ጠንካራ ነበር፡፡

ስለዋንጫ ፉክክሩ

“የሚቀጥለው ጨዋታ ካሉት ውጤቶች አንፃር ሳይሆን በራሱ ይዞት የሚመጣ ፉክክር አለ፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲዳማ ቡና ከጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት አምናም አሸንፈናቸዋል ዘንድሮም አንደኛው ዙር አቻ ነው የወጣነው፡፡ ከዛ ውጪ እንግዲህ የነበረው ታሪክ ብዙም አላውቀውም ግን እንደዚህ ዓይነት የፉክክር ስሜት አለ፡፡ ከዛ ውጪ አሁን በስፋት እየመሩን ነው ያሉት ስለዛ ብቻ ሳይሆን የምናስበው አጠቃላይ ብዙ ነጥቦችን ይዘን የተሻለ ደረጃ ላይ መቀመጥ ነው፡፡ አንድ ቡድን ላይ ብቻ ዝግጅት የምናደርግበት ነገር የለም፡፡

በሁለተኛው ዙር ስለሚያሳዩት መሻሻል

“ከቅርብ ጊዜ በኋላ ጊዜ ያስፈልገኛል። ቡድን ስሰራ ትንሽ ለመረዳትም አንዳንድ ጊዜ ይቸገራሉ ፤ ያው የታየ ነገር ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ግን በሂደት ቀስ በቀስ እየተረዱ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ነው፡፡ ልምምድም ድግግሞሽ ነው ፤ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ነው፡፡ ከድግግሞሽ በኋላ ወደ ጥሩ ነገር ትመጣለህ ለዛ ነው ሁለተኛ ዙር ላይ ጥሩ ሆነን የመጣነው፡፡

ስለሳላዲን ዝውውር

“አዎ ጥሩ ግዢ ነው፡፡ ማለት ሳላዲን ጥሩ ነው። አሁን ብዙ ነገር ነው የሚሰራልህ ስናመጣው እሱ ከሚሰራቸው ስራዎች ባሻገር ሌሎቹን ልጆች ያነሳሳል በሚል ነው፡፡ ከእርሱ ብዙ መማር የሚችሉ ወጣቶች አሉ። አሁን እኔ ሳያቸው ልምምድ ሲያሰራቸው ሁሉም ከእርሱ መማር የሚፈልግ ፣ ለእርሱ በመስጠት አንድ ነገር እንዲሰራ የሚፈልጉ ናቸው ፤ ክብር አላቸው። አምበል ስናደርገው የተጫዋቾቹ የራሳቸው አምበል የነበሩ ሁሉ እሱ ይሁን በሚል ነው አምበል ያደረኩት፡፡ ይሄ ምን ያሳያል መሰለህ ከእርሱ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ጥሩ ነገርም ይወስዳሉ ያላቸውን አክብሮት የሚያሳይ ነው እና ሳላሀዲን ብዙ ነገር ያስተምርልኛል ብዬ አስባለሁ ጥሩ ነው፡፡”