ሪፖርት | የተለየው መከላከያ በሰፊ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል

ኢትዮጵያ ቡና የመከላከያን የመጀመርያ አጋማሽ የጫና ወጀብ መቋቋም በተቸገረበት ጨዋታ አራት ግቦች አስተናግዶ ተሸንፏል።

መከላከያዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሦስት ለውጦችን በመጀመሪያ 11 ተመራጮቻቸው ላይ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ዳዊት ማሞ ፣ ልደቱ ጌታቸው እና ባድራ ሴይላ ወደ ተጠባባቂነት አውርደው በምትካቸው ግሩም ሀጎስ ፣ አዲሱ አቱላ እና እስራኤል እሸቱን በመጀመሪያ ተመራጭነት ሲያስጀምሩ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል በዚህም ኃይሌ ገ/ተንሳይ እና ዊልያም ሰለሞንን አስወጥተው በምትካቸው ገዛኸኝ ደሳለኝ እና ተመስገን ገ/ኪዳንን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታው አስቀድሞ የተጫዋች ተገቢነት ክስ አሲዟል። ምክንያቱ ደግሞ የመከላከያ ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ ደደቢት በሚጫወትበት ዘመን ይጠራበት የነበረው የአባት ስም ሌላ የነበረ በመሆኑ ይጣራልን የሚል ነው።

ከወትሮው በተለየ እጅግ በተሻለ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት መከላከያዎች ባልተለመደ መልኩ በጀብደኝነት በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ አጋማሽ በመላክ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ እንዳይመሰርቱ ከፍ ያለ ጫና አሳድረው ሲጫወቱ አስተውለናል።

በሊጉ ምናልባት ምርጡን አጋማሻቸውን ያሳለፉት መከላከያዎች ገና በማለዳ ነበር በተጋጣሚ አጋማሽ በሚነጠቁ ኳሶች እድል መፍጠር የጀመሩት ፤ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ መሀል ሜዳ ላይ የነጠቀውን ኳስ ያሳለፈለት ተሾመ በላቸው ከሳጥን ጠርዝ ያደረጋት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ የመጀመርያ ሙከራ ነበረች።

ዋና አሰልጣኛቸውን በህመም ምክንያት አጥተው በምትኩ በዮርዳኖስ አባይ እየተመሩ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በ14ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከተነጠቀ ኳስ በተፈጠረ እድል ተሾመ በላቸው ያደረገው ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።


የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ተረጋግተው ኳስ እንዳይመሰርቱ ለማድረግ የታተሩት መከላከያዎች ጥረታቸው በ20ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል ፤ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በአንድ አጋጣሚ ለማጥቃት ከግባቸው ከፍ ባሉበት አጋጣሚ ከገዛኸኝ ደሳለኝ እግር ከተቋረጠ ኳስ የተነሳውን ሂደት አዲሱ አቱላ በግሩም ሁኔታ ከተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተሾመ በላቸው በረከት አማረን አልፎ በማስቆጠር መከላከያዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ታድያ ከግቧ መቆጠር በኋላም ያላባራው የመከላከያ ጫና በደቂቃዎች ልዮነት ሁለተኛ ግብ አስገኝቶላቸዋል ፤ 23ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ለአበበ ጥላሁን ለማቀበል ሲል የተቋረጠበትን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግሩም ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ቢኒያም በላይ ከበረከት አማረ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በግሩም አጨራረስ አስቆጠሮ የቡድኑን መሪነት አሳድጓል።


ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ በመጠኑም ቢሆን ጋብ ያለውን የመከላከያን ጫና ሂደት ተከትሎ ቡናዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው የመመለስ ፍንጭ አሳይተው የነበረ ሲሆን በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ግን ቡድኑ በጣት ከሚቆጠሩ ያልተቀናጁአጋጣሚዎች ውጭ ወደ መከላከያ ሳጥን አካባቢ ለመድረስ ተቸግረው አስተውለናል።

በ39ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ተመስገን ገ/ኪዳን የሰራውን የማቀበል ስህተትን ተከትሎ የተገኘውን ኳስ ተሾመ በላቸው ከሳጥን ጠርዝ ያሳለፈውን ኳስ ተጠቅሞ አዲሱ አቱላ በቀላሉ ባስቆጠራት ግብ መከላከያዎች አጋማሹን 3-0 በሆነ የበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር መከላከያዎች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ የነበራቸው ጫና የማሳደር ፍላጎት በሂደት እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እያደገ እንዲሁም በግራ መስመር በኩል የተሻለ የማጥቃት ጥረት ያደረጉበት አጋማሽ ነበር።

ዊልያም ሰለሞንን ተክተው ያስገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀስ በቀስ በማጥቃት ረገድ የሚታዩ መሻሻሎችን ማስመልከት ጀምረዋል ፤ በ63ኛው ደቂቃ ዊልያም ሰለሞን ያሳለፈለትን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ በላካት እና ክሌመኔት ቦዬ በያዘበት ኳስ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀሪዎቹን የአጋማሹን ደቂቃዎች ሮቤል ተክለሚካኤልን በፊት አጥቂነት በመጠቀም ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተወሰነ መልኩ የተረጋጉ ቢመስሉም የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የተሻለ መነቃቃትን በማሳየት በተለይ በሁለት አጋጣሚዎች ምንተስኖት አዳነ ያመከናቸውን አጋጣሚዎችን ጨምሮ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር የሚረዱ አጋጣሚዎችን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ነገርግን በተጨማሪ ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ላይ በረከት አማረ በሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አሚን ነስሩ የቡድኑን አራተኛ ግብ በማስቆጠር በማጥቃት ረገድ ሲታማ ለከረመው ቡድን አይረሴውን ምሽት ይበልጥ ጣፋጭ ማድረግ ችሏል።


ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ በ24 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥሉ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ቡና በ28 ነጥቦች በነበረበት 7ኛ ደረጃ ቀጥሏል።