“የአዲስ አበባ ነዋሪ አበበ በቂላ ስታዲየም መጥቶ እንዲደግፈን…” አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መግለጫ ሰጥተዋል።

በሕንድ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጪው እሁድ በማጣሪያው ሁለተኛ ተጋጣሚው ደቡብ አፍሪካን በመልስ ጨዋታ ያስተናግዳል። በመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳው ውጪ የ3-0 ድል ያሳካው ቡድን ዋና አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ይህንን ጨዋታ እና የቡድኑን ሰሞናዊ ዝግጅት የተመለከተ መግለጫ ዛሬ ከሰዓት በፌዳሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሰጥተው ነበር።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በማህበራዊ ትስስር ገፆቹ ይፋ ባደረገው የአሰልጣኙ መግለጫ ላይ ምንም የጉዳት ዜና የሌለበት ቡድኑ ከሚያዚያ 10 ጀምሮ በቀን አንዴ ጊዜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እና በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን ሲያደርግ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን በጥሩ የሥነልቦና ደረጃ ላይ ወደ ጨዋታው ዕለት እየተቃረበ ይገኛል።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ ዩጋንዳን ለማለፍ ከበድ ያለ ፈተና ገጥሞት የነበረ መሆኑ ሁለተኛው ጨዋታ ላይም ሊቸገር እንደሚችል ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ከሜዳው ውጪ ደቡብ አፍሪካን በሰፊ የግብ ልዩነት መርታቱ ትኩረትን የሚስብ ነበር። አሰልጣኝ እንዳልካቸው እንዳሉትም ከዩጋንዳው ጨዋታ በመነሳት በክፍተቶቻቸው ላይ መስራታቸው ለውጤቱ መገኘት ምክንያት እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን ስለጨዋታው ያላቸውን ሀሳብ እንዲህ አካፍለዋል። “ከዚህም ስንሄድ የቻልነውን ነገር አድርገን ማሸነፍ ነበር ዓላማችን። እዚህ አዲስ አበባ ላይ ጨዋታውን ማክበድ አልፈለግንም። እዛው ለመጨረስ መከላከል ሳይሆን አጥቅተን ለመጫወት ነበር እዚህም ስንሰራ የነበረው ፤ ያንን አድርገን ወጥተናል። ስለመጣው ውጤት እኔም ልጆቹም ደስተኛ ነን ፤ እግዚያብሄርን ላመሰግን እወዳለሁ። ”

አሰልጣኙ ከመልሱ ጨቃታ በፊት ከቤኒሻንጉል ፓይለት ፕሮጀክት አንድ ተጫዋች ማካተታቸውን ያነሱ ሲሆን ነገር ግን የመልሱንም ጨዋታ በመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾቻቸው እንደሚያደርጉ ፍንጭ ሰጥተዋል። ለዚህም ዋና ምክንያታቸው አሁንም ጨዋታው አልቋል ብለው አለማመናቸው መሆኑ ከአስተያየታቸው መረዳት ይቻላል። “ደቡብ አፍሪካ ላይ የተጫወትነውን ጨዋታ አሁን ረስተነዋል። አዲስ አበባ ላይ የምንጫወተውን ጨዋታ እንደ አዲስ ነው የምንጫወተው። ያመጣነው ውጤት የሚያኩራራ ሳይሆን ይበልጥ የምንዘጋጅበት ነው።”

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ስላደረጉላቸው ድጋፍ ያመሰገኑት አሰልጣኝ እንዳልካቸው በእሁዱ ጨዋታ ደግሞ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተከታዩን ጥሪ አቅርበዋል። “ይህ ጨዋታ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ወሳኝ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ አበበ በቂላ ስታዲየም መጥቶ እንዲደግፈን እና እንዲያበረታታ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።”

የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በድምር ውጤት ደቡብ አፍሪካን ማለፍ ከቻለ ወደ ሕንድ በሚያደርገው ጉዞ ሦስተኛ ተጋጣሚው የሚሆነው የናይጄሪያ አቻው እንደሆነ ታውቋል።