የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ሲዳማ ቡና

ከደቂቃዎች በፊት በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው እንደጠበኩት አይደለም። ጨዋታውን ማሸነፍ ስለምንፈልግ ቶሎ ቶሎ ለማጥቃት እየሞከርን ነበር። ይህንን ተከትሎ ኳሶች የበላሹ ነበር። ባለፉት ጨዋታ ነጥብ መጣላችን የዛሬውን ጨዋታ እንድናሸንፍ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል። ሲዳማም ጠንካራ ቡድን ነው። በጨዋታው ቀድመን ግብ የማግባት ዕድልም አግኝተናል። በመጨረሻ ሰዓት በተፈጠረ የትኩረት ችግር ወዲያው ጎል ሊቆጠርብን ችሏል። ጨዋታውን አሸንፈን የምንወጣበትን ዕድልም በሁለተኛው አጋማሽ አግኝተን ነበር። ነገር ግን አልተጠቀምንበትም።

ስለተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ…?

ሰሞኑን በነበረው እንቅስቃሴ ድክመታችን ወደ ጎሉ ስንደርስ ተጫዋቾቻችን የተረጋጉ አለመሆኑ ነው። ለዚህ ደግሞ የጣልናቸው ነጥቦች አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ሲዳማ ቶሎ ቶሎ አጫጭር ኳስ እየነካ ከተከላካይ ጀርባ ረጃጅም ኳስ በመላክ ሊያጠቁን እንደሚችሉ ገምተናል። እኛ ደግሞ የምናገኛቸውን ኳሶች ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። ዞሮ ዞሮ ለማሸነፍ አልተሳካልንም።

የአዳማ ቆይታህ እንዴት ነበር?

መጥፎ ቡድን አለኝ ብዬ አላስብም። ሜዳ ላይ ጥሩ የሚንቀሳቀስ ቡድን አለኝ። በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ቁጥሮቹን ብታያቸው የተሻልን መሆናችንን ያሳያሉ። ነገር ግን 3 ነጥቡን ማግኘት አልቻልንም። ደረጃችንንም ከፍ የሚያደርገ 3 ነጥብ ነበር። ያንን ማግኘት ስላልቻልን እኔ ቡድኔን ማግኘት የምፈልገው ደረጃ ላይ ነው ብዬ መናገር ይቸግረኛል።

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ጨዋታው ላይ ስለተጎዳው ጊት…?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጥሩ ብቃት ካሳዩት አንዱ ጊት ነው። ስለዚህ ጊት ደግሞ ቡድናችን የተዋጣለት እና የተደራጀ መከላከል እንዲኖረው ካደረጉት መካከል አንዱ እሱ ስለሆነ መጠበቅ ነበረብን። እርሱም እችላለው ብሎ ስለነገረን ነው እንጂ ጉዳቱ የከፋ እስከሆነ ድረስ ማስወጣት አለብን። ከዛም ሊያጫውተው ስላልቻለ መቀየር ነበረብን። መጠበቃችንም ተጫዋቹ ያለውን ጠቀሜታ ከማየት አንፃር ነው።

ስለይገዙ አጨዋወት…?

ይገዙ ከመስመር እየተነሳ ማጥቃቱን ሊቀጥል ይችላል። ሳላዲን ያለውን ልምድ እና አቅም ተጠቅሞ መጫወት ይችላል። እሱ ብቻ ሳይሆን ይገዙም በቦታው መጫወት ይችላል። ስለዚህ ሁለቱም ባላቸው ብቃት መጠቀም ስላለብን ይሄ የግድ ነው። አንዳንድ ጊዜ በ2 አጥቂ በምንጫወትበት ጊዜ የምንጠቀምባቸው ጊዜያቶች ይኖራሉ። ይገዙ ዓምናም ኦኪኪ እያለ ከመስመር ነበር የሚነሳው። ማድረግ የሚገባውን ሀላፊነት በደንብ ከሰጠከው መምጣት ይችላል። በአጠቃላይ ትናንት የነበረው ይገዙ አይደለም አሁን ያለው። በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው።