የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-1 ወላይታ ድቻ

የሊጉ የአዳማ ቆይታ የተቋጨበት ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ጊዜያዊ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“በመጀመሪያው አጋማሽ እንደጠበቅነው አልሄደለንም። ምክንያቱም አዲስ አሰላለፍ ነበር ይዘን የገባነው እና ትንሽ ልጆቹ ግር ብሏቸዋል። ቢተገብሩት የተሻለ የማጥቃት መንገድ ነበር ፤ ግን ጥሩ ስላልነበርን ከዕረፍት መልስ ወደለመድነው አሰላለፋችን ተመልሰን ጥሩ ነገር አድርገን ወጥተናል።

የናትናኤል ቅያሪ ለውጥ ስለመፍጠሩ

“ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ከኋላ ሦስት የመሀል ተከላካዮች ስለነበሩን ሰዒድ በዛኛው ዓለምብርሀን በዚህኛው መስመር እንዲጫወቱ ናትናኤል ገፋ አድርጎ እንዲጫወት ነበር ያደረግነው ተጭነን ለመጫወት። ምክንያቱም 1-0 እየተመራን ስለነበር ተጭነን ግብ አስቆጥረን ማሸነፍ ነበር የነበረብን እና በዛ መልክ ቀይረን ገብተናል።

ድሉ በዋንጫው ፉክክሩ ውስጥ እንዲቆዩ ስለማድረጉ

“እሱ በሂደት የሚታይ ይሆናል። እኛ ከፊት የምናገኛቸውን ተጋጣሚዎች እያሸነፍን መሄድ ነው። በኋላ ላይ የሚመጣውን ውጤት መቀበል ነው።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለሽንፈቱ

“በዚህ ውጤት ይጠናቀቃል ብዬ አላሰብኩም። ከነበረን የ45 ደቂቃ ብልጫ በእንቅስቃሴም በውጤትም ጥሩ ነበርን። ሦስት ነጥብ እናጣለን የሚል ግምት አልነበረኝም። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ የእኛ ልጆች ከልምድ አጨዋወት ውጪ ሆኑብን እና እነሱ ፈጣን የማጥቃት ስራዎቻቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ጎሎች አስቆጥረዋል። በራሳችን ስህተቶች የተገኙ ጎሎች ናቸው ፤ በልምድ አጨዋወት ተበልጠናል ማለት ይቻላል።

ስለጨዋታ ምርጫቸው

“በጥልቀት አልተከላከልንም። እነሱ በመጀመሪያው አጋማሽ ይዘውት የነበረው አሰላለፍ እና በሁለተኛ አጋማሽ የያዙት ልዩነት አለው። እኛ ከጀመርነው አሰላለፍ ልንወጣ አልቻልንም ፤ ብዙ የማጥቃት ቦታዎች ነበሩን መጀመሪያ። ነገር ግን እነሱ መልሶ ማጥቃታቸው ጥሩ ነበር። ከቆሙ ኳሶች በመነሳት ቶሎ በማጥቃቱ የተሻሉ ነበሩ። እኛ ግን በራሳችን የተነጠቁ ኳሶች ነበሩ ሲገቡብን የነበሩት። በአጠቃላይ ከጎሉ በኋላ ተነሳስተዋል ፤ እኛ ደግሞ የአቋቋም ስህተት ነበረብን። በተለይ ተከላካዮቻችን ትንሽ የመረጋጋት ነገር ቢታይባቸው ፤ አጥቂዎቻቸው የማካለብ ነገር ይታይባቸው ስለነበር። አንድ ልምድ ያለው ተጫዋች ከኋላ መስመራችን ላይ ቢኖረን ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ አቅማችን የፈቀደውን አድርገናል። በእኔ ዕምነት በተለይ ተጫዋቾቹ አቅማቸው የፈቀደውን ነገር አድርገዋል። ከዚህ በኋላ የመጣንበትን ነገር ትተን ራሳችንን ከራሳችን ጋር እያነፃፀርን መሄድ ነው። እኛ ከማንም ጋር መወዳደር አንችልም። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ራሳችንን በማየት ውድድሩን ለማጠናቀቅ እንሞክራለን።”