የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የምድብ ድልድል ወጥቷል

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የምድብ ተጋጣሚዎቿን አውቃለች።

በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) አስተናጋጅነት ለሚከወነው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የምድብ ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡ ከግንቦት 14 ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት ይደረጋል በተባለው (የሚጀመርበት ቀን ሊለወጥ ይችላል) እና በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚከናወነው ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በድምሩ ስምንት ሀገራት ተካፋይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ውድድሩ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን የምድብ ድልድሉ የሚከተለው ሆኗል:-

በምድብ 1 ዩጋንዳ ፣ ብሩንዲ ፣ ሩዋንዳ ፣ ጅቡቲ 

በምድብ 2 ኢትዮጵያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን

በተያያዘ ዜና በያዝነው ወር ግንቦት 16 በአዳማ ከተማ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር ውድድር በዚህ የሴካፋ ዋንጫ ውድድር የተነሳ ሊራዘም የሚችልበት ዕድል የሰፋ መሆኑን ሰምተናል፡፡