ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

የጨዋታ ሳምንቱ ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ድንቅ ሆነው በዋሉት አብዱራህማን ሙባረክ እና ሄኖክ አየለ ሁለት ሁለት ግቦች ሀዲያ ሆሳዕናን 4-0 በሆነ ውጤት በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል

ድሬዳዋ ከተማዎች በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ዳንኤል ደምሴ እና ማማዱ ሲዲቤ አስወጥተው በምትካቸው አብዱራህማን ሙባረክ እና አቤል አሰበ ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት አስገብተው ሲጀምሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግም ሦስት ለውጦች ያደረጉ ሲሆን በዚህም ግርማ በቀለ ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና እያሱ ታምሩን በቃለዓብ ውብሸት ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ተክተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን አማካኝነት ባደረጉት እና ፍሬው ጌታሁን በቀላሉ ባዳናት ሙከራ የጀመረው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ የነበረ ፉክክር የታየበት ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማዎች በተጋጣሚ ሳጥን የነበራቸው አፈፃፀም ግን የተሻለ የሚባል ነበር። በዚህም ጥሩ የሚባል አጋማሽን በብዙ መመዘኛዎች ያሳለፉት ድሬዳዋ ከተማዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ገና በማለዳ መሪ መሆን ችለዋል።

በ8ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ አብዱረህማን ሙባረክ በግንባር በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በደቂቃዎች ልዩነትም 11ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ አብዱረህማን ሙባረክ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሰብሮ ከገባ በኋላ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሄኖክ አየለ ተረጋግቶ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት አሳድጓል።

በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ወስደው ለመንቀሳቀስ ሲጥሩ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 20ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታው እንዲሁም በ22ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር። በተወሰነ መልኩ ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለው ጨዋታ በ44ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት ያስተናገደው አበባየሁ ዮሐንስ በእያሱ ታምሩ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽን ሱራፌል ጌታቸውን አስወጥተው በምትኩ ዳንኤል ደምሴን በማስገባት የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጀመሪያው አንፃር ጥንቃቄን መርጠው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ነበር። አጋማሹ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ያዘው መጫወት የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ አጋማሽ ማሳለፍ ቢችሉም ከሳጥን ውጪ ከሚመቱ እና ከሚሻገሩ ኳሶች ውጪ እንደ ቡድን የጠሩ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ እምብዛም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። 

በ55ኛው ላይ ሚካኤል ጆርጅ ከሳጥን ውጪ ያደረጋት እንዲሁም በ80ኛው ደቂቃ በኳስ ምስረታ ሂደት መሳይ ጳውሎስ ከተሳሳተው ኳስ የተነሳውን ማጥቃት ዑመድ ኡኩሪ ያደረጋትን አደገኛ ሙከራ ጨምሮ ፍሬው ጌታሁን በድንቅ ብቃት አድኖባቸዋል። ከመከላከል ባለፈ በተወሰኑ አጋጣሚዎች መልሶ ማጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ65ኛው ደቂቃ ተጋጣሚ ሜዳ ላይ በነጠቁት ኳስ የፈጠሩትን አጋጣሚ አብዱረህማን ሙባረክ መጠቀም ሳይችል ከቀረው አጋጣሚ ባለፈ ከሚነጠቁ ኳሶች ከሀዲያ ሆሳዕና ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ሰፊ ክፍተት መጠቀም የሚያስችሉ ቅፅበቶችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

81ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አብዱለጢፍ መሀመድ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ የነበረው ሄኖክ አየለ በሁለተኛ ሙከራ አስቆጥሮ የድሬዳዋ ከተማን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ ሲያስቆጥር ተደጋጋሚ ዕድሎችን መጠቀም ሳይችል ቀርቶ የነበረው አብዱረህማን ሙባረክ በ91ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የተገኘችን አጋጣሚ በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር የወራጅነት ስጋት ለተደቀነበት ቡድኑ አስደናቂ የነበረውን ጨዋታ በአራተኛ ግብ አሳርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 27 በማሳደግ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በ29 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ቀጥለዋል።