የተካልኝ ደጀኔ ወቅታዊ ሁኔታ…

አመሸሻ ላይ ያለ ጎል በተጠናቀቀው የአዳማ እና አርባምንጭ ጨዋታ ላይ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ተከላካዩ ተካልኝ ደጀኔ በምን ዓይነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አጣርታናል፡፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ቀጥሏል፡፡ በዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታው ላይ ከዕረፍት መልስ የአርባምንጭ ከተማው ተከላካይ ተካልኝ ደጀኔ እና የአዳማ ከተማው አጥቂ አቡበከር ወንድሙ ኳስ ለማግኘት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ግጭት በማስተናገዳቸው ጨዋታው ለአምስት ያህል ደቂቃዎች የተቋረጠበት አጋጣሚ የጨዋታው አስደንጋጭ ክስተት ነበር።

ከሁለቱ ቱጫዋቾች የምላስ መታጠፍ እና ጭንቅላቱ አካባቢ ጠንከር ያለ ጉዳት ያስተናገደው ተካልኝ ደጀኔ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል ሲያመራ አቡበከር ወንድሙ በአንፃሩ ሜዳ ላይ ከተደረገለት ህክምና በመቀጠል ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል፡፡ ይህንን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ የተካልኝ ደጀኔ ወቅታዊ ሁኔታ በምን ዓይነት ሂደት ላይ እንደሚገኝ አጣርታለች፡፡ ተጫዋቹ በሆስፒታል ከተደረገለት ህክምና በኋላ የነቃ ሲሆን ስላለበት ሁኔታ አጭር ሀሳብ ሰጥቶናል፡፡

“አሁን ደህና ነኝ። በሰዓቱ ምን እንደሆንኩ አላስታውስም። ኤም አር አይ ተነስቼ ‘ደህና ነህ’ ተብያለው። አሁን ትንሽ ጭንቅላቴ አካባቢ ስሜት አለው ፤ ነገር ግን ሰላም መሆኔ ተነግሮኛል፡፡” በማለት የነገረን ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ተጫዋቹ ህክምናውን አጠናቆ ክለቡ አርባምንጭ ባረፈበት ሆቴል ከቡድን አጋሮቹ ጋር መቀላቀሉን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ገልፀውልናል፡፡