የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 2-2 አዲስ አበባ ከተማ

በቀትሩ ጨዋታ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ነጥብ ተጋርተው ከወጡ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘራዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

“ዛሬ ጨዋታችን ከባለፉት ሁለት ጨዋታ እንቅስቃሴ ይሻል ነበር። አሁንም በራሳችን ስህተት ነው ጎሎች እየገቡብን ያሉት። እዚህ ጋር ነው ማረም ያልቻልነው። ምክንያቱም ባሉት ልጆች ነው መጫወት የሚቻለው። በተደጋጋሚ የመሐል ተከላካዮች መጎዳታቸው ትንሽ ዋጋ እያስከፈለን ነው። ከዚህ ውጪ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት ይሄዱ ነበር። የጎል አጋጣሚም ፈጥረን አግብተናል። በእንቅስቃሴም ደረጃ ጥሩ ቢሆንም የመሐል ተከላካዮቻችን አካባቢ ክፍተቶች ይታያሉ። ልጆቻችን ድነው የሚመጡ ከሆነ ይስተካከላል።

ስለ ካሉንጂ ሞንዲያ ቅያሪ

“ስህተት ስለሰራ አይደለም። ሁለትም ሊያገባ ይችላል ፤ እሱ አይደለም። ዛሬ እንቅስቃሴው ፣ አቋቋሙ ልክ አልነበረም። ከዛ ውጪ በሦስት ተከላካይ ነበር የጀመርነው። ብዙም ፊት ላይ አስቸጋሪ ስላልነበር ወደ አራት ሦስት ሦስት ነው የቀየርነው። እርሱ በእንቅስቃሴ ጥሩ ስላልነበረ እርምጃ ወስደናል። የታክቲክ ለውጥ ነው።

ስለአዳሙ ቀይ ካርድ

“ ይሄን ለዳኛው ብተው ይሻላል። ምክንያቱም አራተኛ ዳኛ ማረጋጋት ይችላል። ለመምራት ስትወጣ ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ልትቃወም ከሆነ ቡድን ልትመራ አትችልም። እኛም ጋር ስሜታዊ የመሆን ነገር ነበር ፤ እርሱን እናርማለን። ነገር ግን ማረጋጋት እየተቻለ ዳኛን እየጠሩ ሰዓት እየገደሉ ካርድ ቢሰጥ ትርጉም የለውም። ቢጫ ካርድ ቢሰጠኝ ከሜዳ አልባረረም። ስለዚህ ለውጥ የሚያመጣው ነገር የለም እና እኛ እንደምንሳሳተው ሁሉ እነርሱ እርምጃ ላይ ባይፈጥኑ ጥሩ ነው። ካርዱ ምን እንደሆነ ባላቅም አንድ አንዴ ይፈጠራል።”

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – አዲስ አበባ ከተማ

በጨዋታው ደስተኛ ስለመሆናቸው

“ ደስተኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም ላሰለጥን አልመጣሁም። ልጆቹን እንዲነሳሱ በማድረግ ለማጫወት ነው የመጣሁት። ያ ነገር በደንብ ተሳክቶልኛል። በርከት ያለ የጎል ሙከራ ነበር። ስለዚህ አንድ ነጥብ ይበቃኛል ብዬ መናገሩ ትንሽ ቅር ያሰኘኛል።

ስለ አጨራረስ ችግር

“ በሙሉ ተሞክሯል ፍፁም ቅጣት ምቱ ሲሳት ሦስተኛም ድኗል። ስለዚህ ለእኛ ዛሬ ፈጣሪ የወሰነልን አቻ ነበር። ልጆቹ ከጠበኳቸው በላይ ነው የሆኑት። ማስተካከል የሚገባን መሆኑ ግድ ነው። የኳስ ነገር የማይታወቅ በመሆኑ እንጂ በእርግጠኝነት የምናገረው አዲስ አበባ ይወርዳል ብሎ መናገር ሞኝነት ነው።

ስለ ቡድኑ ከፍተኛ እንቅስቃሴ

“በዚህ የሰባት ሰዓት ፀሀይ ላይ እንደዚህ ማየት ፣ ፀሀዩ የቀዘቀዘ ዕለት እነዚህ ልጆች ምን ያደርጋሉ የሚለውን ነገር በደንብ ተገንዝበን አሁንም ልጆቼ ላይ ከስራው ይልቅ ማነሳሳት ላይ ነው የማተኩረው። ምክንያቱም የመጨረሻ ስምንት ጨዋታዎች አዲስ አበባን ለማቆየት ታሪክ ለመፃፍ የሚሆነውን ሁሉ አደርጋለው።”