ሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ለማሰናበት ወስኗል

ከደቂቃዎች በፊት የሲዳማ ቡና አመራሮች ባደረጉት ውይይት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከክለቡ እንዲሰናበቱ መወሰናቸው ተረጋግጧል።

በ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን መለያየት ተከትሎ ነበር የቀድሞው የመከላከያ ፣ ደደቢት ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ 70 እንደርታ አሰልጣኝ የነበሩት ገብረመድህን ኃይሌ ሲዳማ ቡናን በመረከብ ቡድኑን ከመውረድ ስጋት አትርፈውት የነበረው፡፡

የአምናውን ውጤት ተከትሎ ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ለሁለት ዓመታት አብሮ ለመዝለቅ ወስኖ ነበር። ሆኖም የአሰልጣኙ የእስካሁኑ ጉዞ ክለቡ ባስቀመጠው ቅድመ መመሪያ መሠረት እየሄደ አይደለም በሚል ዛሬ በመከላከያ 5-3 መሸነፋቸውን ተከትሎ የክለቡ አመራሮች ባደረጉት ውይይት አሰልጣኙ ከኃላፊነት እንዲነሱ ወስነው ወጥተዋል፡፡

ክለቡ አመሻሽ ላይ ለአሰልጣኙ የመልቀቂያ ደብዳቤ የሚሰጡ መሆኑን የሰማን ሲሆን አሰልጣኝ ገብረመድህንም ክለቡ በባህር ዳር ባረፈበት ሆቴል እንደማይገኙ ተሰምቷል፡፡