ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች በቀዳሚው ዓበይት ጉዳያችን ተዳሰዋል።

👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣል እና የፋሲል ከነማ ማሸነፍ

በጨዋታ ሳምንቱ የተመዘገቡ ውጤቶች በተለይ በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር ላይ የተወሰኑ ለውጦችን ያስከተሉ ነበሩ። ከዚህ ውስጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣል እና የፋሲል ከነማ ማሸነፍ ትኩረት ሳቢ ነበር።

ወላይታ ድቻን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁንም ተሰብስቦ የሚከላከልን ቡድን በማስከፈት ረገድ ውስንነት እንዳለባቸው በሚያሳብቅ መልኩ ጠጣሩን የወላይታ ድቻን መከላከል አወቃቀር መስበር አለመቻላቸውን ተከትሎ ከድቻ ጋር አንድ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል። ይህ የአቻ ውጤት ቡድኑ ከአራት የጨዋታ ሳምንት በፊት ከመከላከያ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ የተመዘገበ ሲሆን የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን በአንድ ብቻ አሳድጎ በ51 ነጥብ እንዲቀመጥ ያስገደደ ነበር።

በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ በነበረው እና በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥተኛ ተፎካካሪ የሆኑትን ፋሲል ከነማዎች ከባህር ዳር ነጥብ ያገናኙበት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በ87ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችው የፍቃዱ ዓለሙ ጎል ፋሲልን ባለድል አድርጋለች። ይህም ማለት ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 43 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 8 ማጥበብ የቻሉበት ሳምንት ሆኗል ማለት ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ከፍተኛ መሻሻል ላይ የሚገኘው መከላከያን የሚያገኙ ይሆናል። በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ጠቋሚ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲገናኙ የነጥብ ልዩነቱ በጥቂቱም ቢሆን መጥበቡ የዛን ጨዋታ ዋጋ ካሁኑ ከፍ ያደረገ ሆኗል።

👉 ከመመራት ተነስተው አስደናቂ ድል ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች

በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል እጅግ አዝናኝ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እስከ 78ኛው ደቂቃ 3-1 ሲመራ ቢቆይም በመጨረሻዎቹ 12 ደቂቃዎች በተገኙ ግቦች ወልቂጤ ከተማን 4-3 በማሸነፍ እስደናቂ ድል አስመዝቦ መውጣት ችሏል።

ገና በመጀመሪያው 20 ደቂቃ በወልቂጤ ከተማዎች የሁለት ግብ የበላይነት የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች አጋማሹን አቡበከር ናስር ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት 3-1 እየተመሩ ነበር የፈፀሙት። በሁለተኛው አጋማሽም እንዲሁ ወልቂጤ ከተማዎች መሪነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሉ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በተለይ ጫላ ተሺታ በሁለት አጋጣሚዎች የተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ጌታነህ ከበደ በአግባቡ ማቀበል ባለመቻሉ ያመከኗቸው ዕድሎች ለቡናማዎቹ ተስፋን የፈነጠቁ ነበሩ።

በሂደት የሁለት ግብ መሪነት የነበራቸው ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ 25 ደቂቃዎች ይበልጥ ለመከላከል ትኩረት መስጠታቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ ኳሱን እንዲቆጣጠሩ እና በጨዋታው በተሻለ መልኩ አስፈሪ በነበረው የቡድኑ የግራ መስመር ማጥቃት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እንዲፈጥሩ አድርጓል። በዚህም ቡናዎች በ78ኛው እና 79ኛው ደቂቃ ላይ በየአብቃል ፈረጃ እና አቡበከር ናስር ግቦች አቻ መሆን ችለዋል።

እነዚህ ግቦች አጠቃላይ የጨዋታውን ግለት (Momentum) ወደ ኢትዮጵያ ቡና እንዲያጋድል ያስገደዱ ነበሩ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም በዛው መጠን ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ89ኛው ደቂቃ እንዲሁ አራተኛ ግብ አክለው ጨዋታው አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስከ 22ኛ ሳምንት ድረስ ኢትዮጵያ ቡና አስቀድሞ ግብ ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው ሦስት ነጥብ (ሦስት አቻ) የነበረ ሲሆን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ላይ እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ላይ ከመመራት ተነስተው የወሰዷቸው ስድስት ነጥቦች የቡድኑ የአዕምሮ ደረጃ ስለመሻሻሉ እና በውድድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት ያላቸው ፍላጎት እያደገ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

👉 ድንቅ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች እና የተዳከመው ሀዲያ ሆሳዕና

በሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠመው ድሬዳዋ ከተማ እጅግ አስደናቂ የሆነ የ4-0 ድልን በመቀዳጀት ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ የሚያደርገውን ውጤት አሳክቷል።

በጨዋታው እንደ ሰሞኑ ሁሉ ድሬዳዋ ፈጣን አጀማመርን ለማድረግ የጣረበት ነበር ፤ በዚህም በተከታታይ ግቦች ገና በ11ኛው ደቂቃ 2-0 መምራት ችሏል። ከግቦቹ በኋላ ሰሞኑን ስንመለከተው እንደነበረው በተወሰነ መልኩ ቡድኑ ተቀዛቅዞ የታየ ሲሆን በዚህኛው ጨዋታ ግን በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን መልሶ ማጥቃቶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን የፈጠረበት ነበር። በዚህም ከ80ኛው ደቂቃ በኋላ ሁለት ግቦችን አክሎ ጨዋታውን በመግደል መውጣት ችሏል።

ብርቱካናማዎቹ በውድድር ዘመኑ በአራተኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን ሀዋሳ ላይ ሲያሸንፉ ሦስት ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ይህኛው ድል ደግሞ በውድድር ዘመኑ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠሩበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኋላ ቡድኑ እያስቆጠራቸው የሚገኙት ግቦች እና የሚቆጠሩበት ደቂቃ ግን አንዳች የመሳሰል ነገር ይታይባቸዋል። በድምሩ በስምንት ጨዋታዎች 10 ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ አምስት (50%) የሚሆኑትን ግቦች ያስቆጠረው በጨዋተው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሲሆን አራት (40%) የሚሆኑት ግቦች ጀግሞ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የተገኙ ነበሩ። ጋዲሳ መብራቴ ጅማ አባ ጅፋር ላይ ያስቆጠራት ግብ ብቻ በ54ኛው ደቂቃ የተመዘገበች ነች።

እነዚህም ቁጥሮች ቡድኑ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ተጋጣሚ በጨዋታው ላይ ራሱን ሳያደላድል ጥቃቶችን በመሰንዘር ግብ የማስቆጠር እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ደግሞ ተጋጣሚ ያለውን የግብ ልዩነት ለማጥበብ ሲውተረተር ለቆ የሚወጣውን ሜዳ በመልሶ ማጥቃት የመቅጣት ሂደቶችን እየተከተለ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

አሁን ላይ ነጥቡን 26 በማድረስ ወደ ላይ ቀና ያለው ድሬዳዋ በቀጣይ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ከአዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በድል መወጣት ከቻለ የሊጉን ቆይታ በሚገባ የተደላደለ ለማድረግ ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ አንፃር ለምስራቁ ክለብ ወሳኝ ይሆናሉ።

በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ዘጠኝ ግቦች የማስተናገዳቸው ጉዳይ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ምቾት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በመከላከልም ሆነ በማጥቃት ጥሩ መዋቅር የነበረው ቡድኑ በዚህ ደረጃ በተከታታይ ጨዋታዎች በቀላሉ ለተጋጣሚው ዕድሎችን የመስጠቱ እና ግቦች የማስተናገዱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ችግር ሆኖበታል።

ከዚህ ባለፈም በማጥቃቱ ረገድ ተደጋጋሚ ዕድሎችን እየፈጠረ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ ችግር ያልነበረበት ቡድኑ አሁን ላይ ግን እንደቀደመው ማጥቃቱን የሰመረ ለማድረግ እየተቸገረ ይገኛል። ይህ ድክመቱ ሳያንሰው ከኋላው ሽንቁሩ መብዛቱ ደግሞ ይበልጥ አደጋ አጋርጦበታል። በተለይም በዚህ ሳምንት ተስፋዬ አለባቸው እና ግርማ በቀለን በቅጣት ማሰለፍ አለመቻሉን ተከትሎ በኋላ ክፍሉ እንዲሁም በአማካይ እና በተከላካይ መስመር መሀከል ከፍተኛ አለመረጋጋት ታይቶበታል። ይህንን ተከትሎም ድሬዳዋዎች ጨዋታውን በፈለጉት መንገድ አስኪደው በሰፊ ጎል እንዲያሸንፉ ሆኗል። ሀዲያ ሀሳዕና በዚህ ድክመቱ ውስጥ ከቀጠለ የድሬዳዋው ሽንፈት ለቀጣይ ተጋጣሚዎቹ የሚያሳየው መንገድ ቡድኑን ይበልጥ ሊያጋልጠው እንደሚችል ዕሙን ነው።

👉 የሰበታ ከተማ ድል እና የወራጅ ቀጠናው መልክ

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ከነበሩት ጨዋታዎች መካከል አንዱ በነበረው እና በሰንጠረዡ ግርጌ በሚደረገው ፉክክር ትልቅ ዋጋ በነበረው ጨዋታ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ከአናታቸው የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ሰበታ ከተማ በመጨረሻዎቹ ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም እንኳን ወሳኙን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ቢቸገርም በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ቡድን ሆኖ የተመለከትን ሲሆን በተለይ ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም አስፈላጊ የሆነውን ግብ ለማስመዝገብ ተቸግሮ ቆይቷል።

ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም ገና ከጅምሩ ፍፁም ማጥቃት ላይ መሰረትን ባደረገ አቀራረብ ተጭኖ በመጫወት ተደጋጋሚ ጥራታቸውን የጠበቁ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ትልቅ ዋጋ ያለው ሦስት ነጥብ አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር ዳግም አዲስ መልክን ተላብሷል። ይህም ከሰሞኑ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥሩ ግለት ላይ የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች የማሸነፍ ግለት ሲገታ በተቃራኒው በሊጉ ግርጌ ያሉት ሰበታ ከተማዎች የራስ መተማመናቸውን የሚያሳድግ ውጤትን ሲያገኙ በነጥብ ደረጃም ሰበታ ከጅማ ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ማጥበብ ችሏል።

7 የጨዋታ ሳምንታት በቀሩት ሊጉ የራሳቸውን የቤት ሥራ ከመወጣት ባለፈ በሌሎች ቡድኖች ነጥብ መጣል ላይ የተመሰረተን የመትረፍ ዕድል የያዙት ሰበታ ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ በኋላ ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ የመቆየት ዕድላቸውን ወደ ገደል አፋፍ እያስጠጉ እንደሚገኝ በማመን “የግድ ማሸነፍ” በሚል የሥነልቦና ሁኔታ ውስጥ ሆነው ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እርግጥ ከዚህ በኋላ በሚደረጉ ጨዋታዎች ቀላል የሚባል ጨዋታ ባይኖርም በአሁናዊ የደረጃ ሰንጠረዥ በሊጉ እስከ አምስተኛ ደረጃ ከሚገኙ እና በተወሰነ መልኩ በውድድር ዘመኑ የተሻለ ወጥነት በማሳየት ላይ ከሚገኙ አምስት ቡድኖች ውስጥ ሦስቱ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ጋር ምን ያህል ጊዜ ይገናኛሉ እንኳን በሚለው ከመዘንን ጅማ አባ ጅፋር እና አዲስ አበባ ከተማ ሦስት ጨዋታዎችን እስከ አምስተኛ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ሲያደርጉ በአንፃሩ ሰበታ ደግሞ አንድ ጨዋታ ብቻ ይጠብቀዋል።

ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በሚገኘው ሊግ እነዚህ ቡድኖች የቤት ሥራቸውን በምን ያህል መጠን ተወጥተው እንዲሁም የሌሎችን መንሸራተት ተጠቅመው በሊጉ ይቆያሉ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 የመከላከያ ሽቅብ መጓዙን ቀጥሏል

ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን በዚህ ሳምንት ያሳካው መከላከያ በማጥቃቱ ረገድ የሚታይን እምርታ ማሳየቱን ሲቀጥል በሰንጠረዡም እንዲሁ ሽቅብ መጓዙን ቀጥሏል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 5-3 በሆነ ውጤት መርታት የቻሉት መከላከያዎች በመጀመሪያ አስራ ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች በድምሩ አስር ግቦችን ብቻ ቢያስቆጥሩም በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ግን ቡድኑ በድምሩ አስራ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ታድያ ይህ የማጥቃት እምርታ በአንድ ወቅት በሊጉ ስላለመሸነፍ ቅድሚያ ሰጥተው ወደ ሜዳ ስለሚገቡ ቡድኖች ስናስብ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን ይመጣ የነበረው ቡድን በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በዚህ ደረጃ አጥቅቶ የሚጫወት ግቦችን ቢያስቆጥርም ግቦቹን ከማስጠበቅ ይልቅ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር የሚታትር ቡድን መሆኑ እጅግ የሚያስደንቅ ለውጥ ነው።

ብዙዎች ምናልባት ይህ ሂደት የአንድ ሰሞን ነገር ይሆን እንዴ ቢሉም ጦሩ በተከታታይ ጨዋታዎች በወጥነት አጥቅቶ የሚጫወት በዚህም ውጤቶችን በማስመዝገብ የብዙዎችን ስጋት ምላሽ እየሰጠ የሚገኝ ቡድን ሆኗል።

በተለይም በአሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ በተመራባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ከወትሮው በተለየ በድፍረት በቁጥር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን እያስገባ ተጋጣሚን ጫና ውስጥ በመክተት እንዲሁም የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ተጋጣሚ ባልተደራጀበት ሁኔታ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ እያሳየ የሚገኘው ሂደት አስገራሚ ሆኗል።

መከላከያዎች 20ኛ ሳምንት ላይ ከባህር ዳር ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በ21 ነጥቦች እና በ6 የግብ ዕዳ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በ30 ነጥቦች እና በአንድ ንፁህ ግብ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብለው መቀመጥ ችለዋል።