ሲዳማ ቡና ጊዜያዊ አሰልጣኙን መርጧል

አመሻሹን ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር የተለያየው ሲዳማ ቡና ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኙን አሳውቋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታው በመከላከያ 5-3 የተረታው ሲዳማ ቡና ዋና አሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ‘ክለቡ በጠበቀው የውጤታማነት መንገድ መሰረት እየተጓዙ አይደለም’ በሚል ከኃላፊነት ለማንሳት መወሰኑን ዘግበን ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችሁ መረጃ መሠረት ደግሞ በይፋ አሰልጣኝ ገብረመድህን ከክለቡ ጋር የተለያዩ ሲሆን የአሰልጣኙ ረዳት በመሆን የቆየው ወንድማገኝ ተሾመ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት (ለሰባት ጨዋታዎች) እንዲመራ ተመርጧል፡፡

የቀድሞው የሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ወንድማገኝ እግርኳስን ካቆመ በኋላ የሲዳማ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የዋናው ቡድን ረዳት ሆኖ ያለፉትን ስምንት ወራት ሲሰራ ቆይቷል፡፡