“በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚሰጠኝን ዕድል መጠቀም ላይ ነው እያተኮርኩ ያለሁት” ዳግም ተፈራ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየታዩ ካሉ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ ከሆነው ወጣት ጋር ቆይታ አድርገናል።

የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን በቅርበት ለተመለከተ በየቡድኖቹ መልካም ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙ ወጣት ግብ ጠባቂዎች መኖራቸው ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ራስ ምታት ለሆነባት ለዚህ ኃላፊነት የሚሆኗትን ተጫዋቾች ልታገኝ እንደምትችል ቢያስብ አያስገርምም። ከእነዚህ ተስፋዎች ውስጥ ደግሞ ዘንድሮ በአመዛኙ በወጣቶች ተገንብቶ በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል በዘለቀው ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ተፅዕኖው እየጎላ የመጣው ዳግም ተፈራ አንዱ ነው።

ዳግም የጋናዊው መሀመድ ሙንታሪን በቅጣት እና ጉዳት አለመኖር ተከትሎ ለሀዋሳ በተሰለፈባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ ኃይቆቹ ሊሸነፉ የሚችሉባቸውን አንዳንድ ጨዋታዎች የተቃራኒ ቡድንን ጥቃት አድፍጦ በመመከት ቡድኑን ታድጎ ሲወጣ ተመልክተናል፡፡ በተጠናቀቀው የ23ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ተዳክሞ በተስተዋለበት እና ከአዲስ አበባ ከተማ ብርቱ ትግል ገጥሞት 2-2 ባጠናቀቀው ጨዋታ ላይ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ትልቅ ሚና ተወጥቷል።

ከጨዋታ እንቅስቃሴ በተጨማሪ አዲስ አበባን ባለድል ያደርግ የነበረውን የሪችሞድ ኦዶንጎን ፍፁም ቅጣት ምት በሁለት ተከታታይ አጋጣሚ መመለሱ ደግሞ እጅግ ያስወደሰው አጋጣሚ ነበር። ዳግም ይህንን ክስተት እንዲህ ሲል ይገልፀዋል። “ከሁሉ በፊት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንደምመልስ ውስጤ ነግሮኝ ነበር ፤ ማድረግ እንደምችልም አውቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከልጅነቴም ጀምሮ ፔናሊቲዎችን የማዳን ልምዱ ነበረኝ ፤ በተለይ የመጀመሪያውን። ሁለተኛውን ግን አላሰብኩትም ነበር፡፡ ሁለተኛውን ኳስ ሲመታ ያለኝን ኃይል እና አቅሜን ነው የተጠቀምኩት፡፡ ቡድኔን ታድጎ ለመውጣት ያደረኩት ጥረት አስደስቶኛል፡፡ በሰዓቱ ስሜቱ በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡” ይላል።

‘ቻቺ’ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ዳግም ተወልዶ ያደገው ሀዋሳ ፒያሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ እግርኳስን የጀመረው የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ የታቦር ፕሮጀክት ውስጥ በመታቀፍ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሆኖ ነበር፡፡ ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ፕሮጀክት ውስጥ በመጫወት ላይ እያለ ለሀዋሳ እና የደቡብ ክልል የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ሲሰለፍ ከነበረበት የተከላካይ ስፍራ ይልቅ ወደ ግብ ጠባቂነት ሽግግር በማድረግ አሁን መድረስ የቻለበት ደረጃ ላይ ለመገኘት ሀ ብሎ መንገዱን ጀምሯል፡፡

ዳግም 2005 ለመላው ደቡብ የወጣት ምርጥ ቡድን ውስጥ ተመርጦ ክልሉን ወክሎ ሻሸመኔ ላይ በነበረ ውድድር ላይ ሲጫወት በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ መልማዮች ዕይታ ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የሦስት ዓመታት የሥልጠና ጊዜን ያሳለፈው ተጫዋቹ አንድ ቀሪ ዓመት እየቀረው የክለብ ህይወትን ለመጀመር በማሰብ ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጥሪ መሰረት በ2009 የሀዋሳ ከተማን ከ20 ዓመት በታች ቡድን መቀላቀል ቻለ፡፡ ከቡድኑ ጋር በዛው ዓመት የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማሳካት ሲችል የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂነት ክብርን አሳክቷል።

በመጀመሪያ የታዳጊ ቡድን ቆይታው እነኚህን ክብሮች ማግኘት የቻለው ተጫዋቹ በቀጣዩ ዓመት በ2010 ጅማሮ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ዋናውን ቡድን ተቀላቀለ። በቀጣዩ የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ዘመን ከሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ተክለማሪያም ሻንቆ እና አላዛር መርኔ ጋር የቡድኑ ግብ ጠባቂ የሆነው ዳግም የተሻለ የመሰለፍ ዕድል እንዲያገኝ በ2011 በውሰት ወደ ዲላ ከተማ የሄደ ሲሆን ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስር
“ራሴን በትልቅ ደረጃ መገኘት እንደምችል ያሳየኝ ትምህርት ቤት ሆኖኛል” ብሎ የሚገልፀውን ዓመት አሳልፏል።

ግብ ጠባቂው 2012 ላይ በሌላኛው የከፍተኛ ሊግ ቡድን ደቡብ ፖሊስ ውስጥ ከቀድሞው የታዳጊ ቡድን አሰልጣኙ ተመስገን ዳና ጋር በመገናኘት ውድድሩ በኮቪድ 19 እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ቆይታን አድርጓል፡፡ በቆይታው ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን ማሳየት በመቻሉ ተመራጭ እየሆነ መምጣት ሲችል ከልጅነት ክለቡ ሀዋሳ ጥሪ ደረሰውና 2013 ላይ በመመለስ በድጋሚ ዋናውን ቡድን መቀላቀል ችሏል፡፡ ሆኖም አምና በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ የተመለከትነው ሲሆን ዘንድሮ ግን ራሱን በትልቅ ደረጃ የሚያሳይበት ዕድል ተከፍቶለታል።

የዘንድሮው የውድድር ዓመት 12ኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ቀዳሚ ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ 26ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ዳግም ተቀይሮ መግባት ችሏል። ይህንን ጨምሮ በዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ መሰለፉን የቀጠለው ተጫዋቹ እስካሁን በአጠቃላይ ለ784 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ መቆየት ሲችል በአራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ በተከታታይ ሳምንታት አስመርጦታል። ዳግም ይህንን የዘንድሮውን ስኬቱን ሲያስብ ምስጋና ማቅረብ ይቀናዋል። “በመጀመሪያ የድንግል ማርያምን ልጅ ነው የማመሰግነው። በመቀጠል አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡ ዘንድሮ የተለየ ነገር ላሳይ የቻልኩበት ሚስጥሩ እግዚአብሔር ስለረዳኝ ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ አሰልጣኝ ዘርዓይ በእኔ ዕምነት ስላለው ነው፡፡ እኔም ያገኘውትን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀምኩበት እገኛለሁ፡፡ ለእኔ መሻሻል እና መለወጥ ደግሞ አሰልጣኛችን አዳሙ ኑመሮንም አመሰግነዋለሁ፡፡ የሚሰጠኝን ልምምድ እና ምክር በአግባቡ እወጣለሁኝ፡፡ አንድ ለአንድ ከተጫዋች ጋር ስንገናኝም ሆነ እንዲሁም ጨዋታን እንዴት አድርገን ተቆጣጥረን እንደምንወጣ ልምምድ ላይ እንማራለን እና የሥልጠናው ሁኔታም ላለሁበት አግዞኛል።”

በወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የሥልጠና ጊዜው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ጥሪ ደርሶት በመጨረሻም ከቡድኑ ስብስብ ውጪ የነበረው የግብ ዘቡ ከሁለት ዓመት በፊት በሴካፋ ዋንጫ ላይ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካቶ ሀገሩን አገልግሏል፡፡ አሁን ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከሚያሳየው አቋም በመነሳት ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ማገልገልን ያልማል፡፡ “የእያንዳንዱ የእግርኳስ ተጫዋቾች ምኞት ሀገሩን ማገልገል ነው ፤ እኔም አቅሙ አለኝ። ጊዜው አሁንም ላይሆን ይችላል ወደ ፊት ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር በፈቀደበት ወቅት ግን ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ላይ ግን ትኩረቴ በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚሰጠኝን ዕድል መጠቀም ላይ ነው እያተኮርኩ ያለሁት፡፡ ፈጣሪ በፈቀደ ሰዓት ደግሞ ሀገሬን ማገልገል እንደምችል አምናለሁ።” ይላል።

በመጨረሻም ለደረሰበት ደረጃ ላይ በህይወቴ ድርሻ አላቸው ያላቸውን በማመስገን ሀሳቡን ይቆጫል፡፡ “እዚህ ለመድረሴ በጣም ብዙ ሰዎች ከጎኔ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የድንግል ማርያምን ልጅ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ቤተሰቦቼ በጥሩም በመጥፎም ከአጠገቤ ስለነበሩ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በሥልጠናው ዓለም ላይ ደግሞ ያለፍኩባቸውን አሰልጣኞች በተለይ አሁን ላይ ዕድል እየሰጠኝ ያለውን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ፣ አዳሙ ኑሞሮን እና ከልጅነት ይሄን ሙያ እንድወደው አድርጎ ላሳደገኝ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከፍ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡”