የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ኢትዮጵያ ቡና

የ24ኛ ሳምንት የረፋዱ የመጀመርያ ጨዋታ በሀዲያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ጎል ሳይቆጠርባቸው ስለመውጣታቸው

“ በእርግጥ እዚህ ባህር ዳር ከመጣን ጀምሮ ውጤት የለንም። በሁለት ጨዋታ ተሸንፈናል። ዛሬ ደግሞ ተጋጣሚያችን ቡና እንደመሆኑ መጠን መጀመርያ እንደምንጫወተው ከፍተን የምንጫወት ከሆነ የዛኑ ነገር እንደሚገጥመን አውቀን ነበር። ለእነርሱ መጫወቻ ሜዳውን ፈቅደን፣ እኛ ደግሞ አሁን ካለንበት መንፈስ ውስጥ ለመውጣት ግዴታ ነጥብ ያስፈልገናል። እየዘጋን ማሸነፍ ነበር የፈለግነው። እርሱ ተሳክቶልናል።

በተደጋጋሚ አሰልጣኝ ካሳዬን ስለማሸነፋቸው

“በእርግጥ አራት ጊዜ ስታሸንፍ ያለ ምንም ፎርሙላ አይሆንም። ሜዳ ለይ እንደ አሰልጣኝ የእርሱን ቡድን ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም እያየው ነው ልዘጋጅ የምችለው። ግን አራት ጊዜ ባሸንፈውም ካሳዬን እበልጣለው ማለት አይደለም። ሜዳው እና ጨዋታው የሚፈቅደውን ስለሆነ ማሸነፍ ስላለብን ተዘጋጅተን እንመጣለን እንጂ ሌላ የተለየ ነገር የለውም። በነገራችን ላይ የኳሳዬ አጨዋወት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ምሳሌ ሊሆን የሚችል በመሆኑ በጣም ደሰ ይለኛል።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች

“ ቡድናችን አዳማ ላይ በጨዋታም ፤ በውጤትም የተሻለ ነበር። እዚህ ከመጣን በኋላ የሜዳውን አጠቃቀም ፣ ስፋቱንም ትንሽ መቆጣጠር ትንሽ ተቸግረን ነበር። ዛሬ ግን ከሌሎች ቡድኖች እያየን በፊት ከምንጫወትበት አራት ሦስት ሦስት አሁን አራት አምስት አንድ ሳምሶም እና ተስፋዬን ቆመው እንዲጫወቱ አድርገናል። ለዚህም ነው ለቀጣይ ጨዋታ ዛሬ ማሸነፍ ዕድሎች ይኖሩናል። አሁን ካለንበት ደረጃ ከፍ ማለት ስላለብን እና ከሁለት ቤት ወደ ሦስት ቤት ስለገባን ለቀጣዩ የተሻለ ነገር ይፈጥርብናል ብዬ አስባለው።”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ክፍት ሜዳ ስለማግኘት

“እኛ ሜዳ ላይ ቦታውን ይከለክሉናል ብለን ነበር ያሰብነው አንደኛ ዙር ከመጡበት አንፃር ፤ ግን እንደዛ አልነበረም። ቦታውን አግኝተነው ነበር። ከእኛ ሜዳ ለመውጣት አስቸጋሪ አልነበረም። እነርሱ ሜዳ ከገባን በኋላ ግን አብዛኛው የተጫዋቾች ቁጥር አስር ፣ ዘጠኝ አድርገው ነበር የሚጫወቱት። በዚህ ውስጥ ቦታውን አግኝተን የጎል ዕድል ለመፍጠር ነበር ፤ ባሰብነው ልክ አልተሳካም። ግን ልጆቹ ያድጉት ነገር ጥሩ ነው።

ስለሜዳው አጠቃቀም

“ጥሩ ነው። ሜዳው ወደ ጎን ያለው ስፋት በቀላሉ ለመታፈን የሚያመች አይደለም። ያን ሜዳ በተቻለ መጠን ባላሱን ጠብቀን ለመጫወት ሞክረናል ግን አብዛኛው የሀዲያ ተጫዋቾች ራሳቸው ሜዳ ነው ያሉት ስለዚህ በቀላሉ ክፍት ሜዳ ለማግኘት ልጆቹ የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል።

ስለ ሽንፈቱ

“እኛ ሁልጊዜ ታሳቢ የምናደርገው የምንጫወትበትን መንገድ ነው። ይሄም ወደ ተሻለ ነገር ያደርሰናል ብለን ትኩረት ስለምናደርግ። ጎን ለጎን ያለንበትን ደረጃ ማሰባችን አይቀርም። ያን ስናስብ እንዴት ነው ከፍ የምንለውን ስንል የምንጫወትበትን መንገድ ነው። ስለዚህ እዛ ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው።

ስለ ዳኝነት ውሳኔ

“የመጀመርያው ጎል ምን አልባት በኋላ የሚረጋገጥ ይሆናል። ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ሚካኤል ጆርጅ ኳሱን በእጁ ነው ያቆመው። ለመስመር ዳኛው ይታየዋል፣ የሚካኤል አቋቋም ለዋናው ዳኛው ላይታይ ይችላል። መስመር ዳኛው ይታየዋል ማስቆም ነበረበት። ከዚህ ውጪ መጨረሻ ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ ዳኛው አቡበከርን በጣም ፀያፍ ስድብ ሲሳደብ ሰምቼዋለው። ምን አልባት አቡበከር ሰድቦት ይሆናል አላውቅም። ዳኛው ህጉ በእጁ ነው ያለው። የፈለገውን መወሰን ይችላል። እንደዚህ ያለ ምልልስ ውስጥ መግባት የሙያው ስነ ምግባር ያልጠበቀ ነው። እኔ በጆሮዬ ሰምቸዋለው ሲሳደብ። ይህ ተቃውሞ ነበረን።”