ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ከተከታታይ ሽንፈት አገግሟል

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ኢትዮጵያ ቡናን በሳምሶን ጥላሁን ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማሸነፍ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት መልስ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

በድሬዳዋ ያልተጠበቀ ሰፊ ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ባደረጓቸው ስድስት ለውጦች ያሬድ በቀለ ፣ ሄኖክ አርፊጮ ፣ ቃለዓብ ውብሸት ፣ አበባየሁ ዮሐንስ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ዑመድ ኡኩሪን አስወጥተው በምትካቸው መሳይ አያኖ ፣ ግርማ በቀለ ፣ እያሱ ታምሩ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ራምኬል ሎክ ቀይረው ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ወልቂጤን ከመመራት ተነስቶ የረታው ስብስብ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደረጉ ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

እጅግ የተቀዛቀዘ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሀል ሜዳ ያመዘነ ነበር። በቁጥር በርከት ብለው መሀል ሜዳ ላይ ያለውን የጨዋታ ሂደት ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በነፃነት ኳስ ይዘው እንዳይወጡ ማድረግ የተዋጣላቸው ነበሩ።

ምንም ዓይነት የግብ ሙከራ ለማሳየት በተቸገረው ጨዋታው የመጀመሪያ የጨዋታው ሙከራ ወደ ግብ የተቀየረች ነበር። 22ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሳ ከራሱ አጋማሽ የላከውን ኳስ ከተከላካዮች ሾልኮ ቡና ሳጥን ውስጥ ሚካኤል ጆርጅ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲልክ አበበ ጥላሁን ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ሀዲያዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ሳምሶን ጥላሁን በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ጨዋታው ከውሃ ዕረፍት ሲመለስ እንደቀደሙት ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የተጨናናቀ ሂደት የተመለከትን ሲሆን በውስን አጋጣሚዎች ግን ሁለቱ ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በርከት ብለው ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

በሙከራዎች ረገድ ደካማ በነበረው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ አነስተኛ ድርሻ የነበራቸው ሀዲያዎች በአጋማሹ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ በተነፃፃሪነት የተሻሉ ነበሩ። በአንፃሩ የተሻለ የኳስ ድርሻ የነበራቸው ቡናዎች በአጋማሹ አብነት ደምሴ በ35ኛው ደቂቃ ካደረጋት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ከጅማሮው አንስቶ በጥንቃቄ ከኳስ ውጪ ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል በተወሰነ መልኩ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የጨዋታ ዕቅዳቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል።

በ62ኛ ደቂቃ ላይ አጨቃጫቂ በነበረች ሂደት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ ለመመስረት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ በረከት አማረ ወደ ግራ ለማቀበል ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ጫና ለማሳደር ወደ በረከት እየሮጠ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ ኳሷን ተደርቦ ወደ ግብነት የተቀየረችበት አጋጣሚ ቢፈጠርም መሀል ዳኛው ከረዳቶቻቸው በመነጋገር ግቧን ሳያፀድቋት ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ሁሉ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ቢሆንም ወደ ፊት በመድረስ ዕድሎችኝ ለመፍጠር ተቸግረው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተቻላቸው መጠን ለማጥቃት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግር የሀዲያ ሆሳዕና የመከላከል አወቃቀር በቀላሉ የሚሰበር አልሆነላቸውም።

በአጋማሹም የተሻለ የነበረችው አማራጫቸው በ86ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር በግል ጥረት ከግርማ በቀለ ጋር ታግሎ ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ በአማኑኤል አመቻችነት በነፃነት ያገኘው አስራት ቱንጆ አደገኛ ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች።

ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕናዎች የ1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 32 በማሳደግ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ34 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ቀጥቸዋል።