የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-2 ሰበታ ከተማ

ሰበታ ከተማ የረፋዱን ጨዋታ በድል ካጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።ጮ

አሰልጣኝ ብርሃን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ከስጋት እየወጡ ስለመሆናቸው

“ጅምር ነው ገና ይቀራል። አሁንም እዛው ግርጌ ላይ ስላለን ቀጣይ ጨዋታዎች ይወስናሉ። ሆኖም ግን የዛሬው ውጤት ግብዓት ይሆነናል ፤ ለቀጣይ ጨዋታ መነሳሳት ይሆናል።

ስለጨዋታ ዕቅዳቸው

“እነርሱ በቀኝ በኩል አድልተው እንደሚመጡ እናውቃለን ፤ በጫላ በኩል ጌታነህን ትኩረት ያደረገ እንደገና ደግሞ መሐል ላይ አብዱልከሪምን። እነዚህ ቁልፍ ተጫዋቾች ተጠንቅቀን ጎል ማስቆጠር እንደምንችል ተነጋግረናል። ሰርተነው የመጣነው ስለሆነ ተሳክቶልናል።

ውጤቱ በሥነልቦናው የሚኖረው አስተዋፅኦ

“ በማሸነፍ ውስጥ አንዳንድ ስሜቶች ይኖራሉ። ወደፊት ስራህን አጠንክረህ እንድትሰራ ያደርግሀል። ይሄ ደግሞ የሚያዘናጋ ሳይሆን ቀጥሎ ያለውን ጨዋታ ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚያሰናዳህ እንጂ አለቀበት ብለህ የምትቆምበት አይደለም።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች

“ታጋጣሚዎቻችን ነጥቡን ፈላጊ ናቸው። የምናገኛቸው ቡድኖች በመውጣት እና በመውረድ ላይ የሚገኙ ናቸው። በመሀል በእግርኳስ የሚሆነው ነገር አይታወቅም ፤ ለማሸነፍ ተግተን እንሰራለን።

ስበታ በሊጉ ስለመቆየቱ

“እርግጠኛ መሆን አይቻል። ግን ጥረትህ ያንን ሊያመላክትህ ይችላል ፤ እንጂ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።”

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“የመጀመርያው 45 ያለንን አቅም ተጠቅመን መጫወት ነው የፈለግነው። ነገር ግን የፈጠርናቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም። ሁለተኛው ላይ በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘን ነበር። ምክንያቱም መጀመርያ ላይ የነበረን ፍጥነት አቀዛቅዞናል። ያንን ክፍተት እነርሱ ተጠቅመዋል።

ውጤት ስለማስጠበቅ መቸገር

“ያለፉትን ቀናት በዚህ ዙርያ ስንነጋገር ነበር። በተወሰነ መልኩ ዛሬ ልናርመው ፈልገናል። ነገር ግን ካገቡ በኋላ ጊዜ አልሰጡንም። የጨዋታ መቆጣጠር ችግር ሳይሆን በገባው ጎል መካከል ያለው ጋፕ ጠባብ ስለነበር ነው።

የጎል አጋጣሚዎች ስለመጠቀም

“ አልተጠቀምንም ፤ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ መረጋጋት ይጎለን ነበር። ያገኘናቸውን ዕድሎች ተጠቅመናል ብዬ አላስብም ፣ መጠቀም የሚቻል ቢሆን ነሮ ጨዋታውን መግደል ይቻል ነበር።

የጨዋታው ወሳኝ አካል

“ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የነበረን መቀዛቀዝ ነው። ካዛ ውጪ ጨዋታውን ተጭነናል ፤ የተሻልን ነበርን። በሁለተኛው አጋማሽ በከፍተኛ ፍጥነት መጫወት አልቻልንም።

ስለመውረድ ስጋት

“ምንም የሚያሰጋን ነገር የለም። ያለንን ነገር እያሻሻልን መሄድ ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው ፤ ስጋቱ እኛ ጋር የለም።