የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-1 ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና በሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ካሳካ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ – ሲዳማ ቡና

ስለ ድሉ

“ጨዋታው ሁለት ዓይነት መልክ ነበረው፡፡ የመጀመሪያው 45 እጅግ በጣም የተሻልንበት እና ተጭነን የተጫወትንበት ነበር፡፡ ሁለተኛው 45 ትንሽ የመቆራረጥ ሂደቶች ነበሩ፡፡ ያንን አስጠብቀን በመውጣታችን ደስ ብሎኛል፡፡

ስለ ዳኝነቱ

“ዳኝነት የራሳቸው ህሊና የሚፈርደው ስለሆነ ፣ እንዲህ እንዲህ ነው ማለቱ ብዙ አያስፈልገኝም፡፡

ስለ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ

“ልጁ ላይ አምኜበት ነው ያደረኩት ስለዚህ ልጁ ያሳየው ፐርፎርማንስ ደስ ይላል፡፡ በቀጣይ የተሻለም ከሆነ እያየን የምንሄድ ይሆናል፡፡

በቡድኑ የተለየው ነገር

“በማጥቃቱ ላይ አሁንም ትንሽ ችግሮች አሉ፡፡ በሂደት እየፈታን እንሄዳለን፡፡”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለ ዘጠና ደቂቃው

“በእኛ በኩል ከነበረብን ክፍተት አንፃር ፣ ከነበረን የስኳድ ጥበት እና ስፋት አንፃር አሉን የሚባሉ ተጫዋቾችን ለማጫወት ሞክረናል፡፡ በአብዛኛው ወጣት ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ ነባር ተጫዋቾችንም ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ እንቅስቃሴው ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ሁለተኛው 45 ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ሲጠቃለል ግን እግር ኳስ አንዳንድ ጊዜ ትችትም አስፈላጊ ነው ብዬ ነው የማምነው። ማናችንም ቢሆን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ሁላችንም አስተዋፅኦ እያደረግን ነው ያለነው፡፡ በተረፈ ግን ዋናው ብዬ የማስበው የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት በፍፁም የሚያሰጥ አልነበረም፡፡ ዳኛው ሚዛናዊ ዳኝነት ሰጥቶናል ብዬ አላስብም። ማንም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያየው ይችላል፡፡ በረኛው እና እንድሪስ ምንድነው ልዩነታቸው ? እኩል ነው ቆመው የነበሩት ፤ ወጥቶ ነው ያዳነው ኳሱን። በሥነ ስርዓት ለመዳኘት ቢሞክሩ ደስ ነው የሚለኝ፡፡ ከጎን መስመር ዳኞች አሉ ይሄ መስተካከል መቻል አለበት፡፡ ዕኩል መዳኘት መቻል አለብን፡፡ የእኛ ክለብም በጀት መድቦ ነው የሚጫወተው፡፡ እንደ ጥረታችን ማግኘት አለብን፡፡ አስተያየት ለመቀበልም መሞከር አስፈላጊ ነው፡፡ ዛሬ እኔ ሚዛናዊ ዳኝነት ነበር ብዬ አላስብም፡፡

የቃል ኪዳን ጉዳት እና ስለ ወጣት ተጫዋቾች

“ጥሩ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ሦስተኛ አጥቂያችን ነው ፤ ሦስቱ አጥቂዎች ከአሁን በኋላ በጉዳት ሜዳ ላይ የሉም ፤ ጉዳቶች እየበዙብን ነው ያሉት ፤ አመራጭም የለንም፡፡ ዛሬ ወጣቶቹ ገብተው ያሳዩት እንቅስቃሴ ቀላል የሚባል አይደለም ፤ እንደ መጀመሪያ ጨዋታ። ስለዚህ ባሉን ወጣት ተጫዋቾች ቀሪውን ጨዋታዎች በጥንቃቄ ብስለት በተሞላበት መንገድ ለመጫወት እንጥራለን፡፡”