ሉሲዎቹ የመጀመርያ ልምምዳቸውን አድርገዋል

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆኑት ሉሲዎቹ የመጀመርያ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 4 ቀን ለሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ለሚጠቀሟቸውን 23 ተጫዋቾች ከቀናት በፊት ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል። ቡድኑ ዛሬ ማረፊያውን በጁፒተር ሆቴል በማድረግ ጥሪ ከተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል አንድ ተጫዋች ሳትገኝ 22 ተጫዋቾችን በመያዝ ረፋድ ላይ በ35 ሜዳ የመጀመርያ ልምምዳቸውን ሰርተዋል። የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች የሆነችው የድሬዳዋ ተከላካይ ብርቄ አማራ በተለያዩ ምክንያቶች ልምምድ ላይ ያልተሳተፈች ሲሆን ዛሬ ቡድኑን በመቀላቀል ነገ ልምምድ ትጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል።

ለአንድ ሰዓት ተኩል በፈጀው የሉሲዎቹ ልምምድ በዋናነት ኳስን መሰረት ባደረገ መልኩ ፈጠን ያሉ ቅብብሎችን መከወን ፣ የቅንጅት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በመስራት ተከውኗል። ለቀናት በዚህ መልኩ የሚቀጥለው የሉሲዎቹ ልምምድ በስተመጨረሻ 23 ወይስ 20 ተጫዋችን ወደ ዩጋንዳ ይዞ በመሄድ ይጠናቀቃል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ በምድብ ለ ከታንዛንያ ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል።