ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው የዓበይት ፅሁፋችን ትኩረት የሳምንቱ ሌሎች ጉዳዮች የቀረቡበት ነው።

👉 ውሃ ሰማያዊው ግድግዳ – ዘንባባ

ውድድሩ ወደ ውቢቷ ባህር ዳር ከተማ ማምራቱን ተከትሎ በተለይ ባለሜዳው ባህር ዳር ከተማ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እጅግ አስደናቂ የሆነ የሜዳ ላይ ድባብን እየተመለከትን እንገኛለን።

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም በዋናነት ሦስት የተመልካቾች መቀመጫ ስያሜዎች አሉ። ከክቡር ትሪቡን ፈት ለፊት ያለው የተመልካቾች መቀመጫ በላይ ዘለቀ የሚል መጠርያ ያለው ሲሆን ከግቦቹ በስተጀርባ ያሉት ሁለት መቀመጫዎች ደግሞ ጣና እና ዘንባባ የሚል ስያሜ አላቸው። በተለይ በስታዲየሙ ከክቡር ትሪቡን በቀኝ ወገን በሚገኘው እና በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም አጠራር ዘንባባ በተሰኘው የተመልካቾች የመቀመጫ ክፍል የምንመለከተው የደጋፊዎች የድጋፍ ድባብ ግን እጅግ የተለየ ነው። የክለቡ ቀንደኛ ደጋፊዎች የሚቀመጡበት ይህ የመቀመጫ ክፍል ለመታደም የክለቡ መለያን መልበስ የግድ ይላል። ከዚህ የተነሳ ይህኛው የሜዳ ክፍል እጅግ ያማረ እና በጥሩ የቀለም ስብጥር ዕይታን የሚገዛ የተለየ ገፅታን ተላብሶ እንመለከታለን።

በቁጥር በርከት ያሉ የክለቡ ደጋፊዎች ተሰብስበው የሚገኙበት ይህ ውሃ ሰማያዊ ግድግዳ ታድያ በጨዋታዎች ወቅት የቡድኑ ዋነኛ የድጋፍ ድምፅ ምንጭ ሲሆን በጨዋታ ወቅትም ሆነ በአንዳንድ በማህበራዊ ትስስር ገፆች በሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መመልከት እንደሚቻለው እጅግ የተለየ ስሜት ያለው የድጋፍ ሁኔታ ከዚሁ የስታዲየሙ ወገን እንመለከታለን።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ባህር ዳር ከተማ አዳማን ሲገጥም ባለ ሜዳ ቡድን በመሆኑ እነዚህ የክለቡ ቀንደኛ ደጋፊዎች በግራ ወገን በሚገኘው ጣና የተመልካቾች መቀመጫ በኩል ተቀምጠው ተመልክተናል።

👉 ዳኝነት ጉዳዮች

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ትኩረት የሳቡ አጋጣሚዎች ነበሩ።

አልቢትር ሚካኤል ጣዕመ በመሩት ጨዋታ በጨዋታው ብቸኛ ግብ የተቆጠረችበት የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ ላይ ሚካኤል ጆርጅ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል ክርክሮች የነበሩ ሲሆን ዳኛው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም እንዲሁ የኢትዮጵያ ቡናውን አጥቂ አቡበከር ናስርን አፀያፊ ስድብ ተሳድበዋል በሚል በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። ዛሬ በወጣው ዜናም የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በአርቢትሩ ላይ ምርመራ በማድረግ ከውድድሩ እንዲሰናበቱ አድርጓል። እርግጥ ይህ ድርጊት ሁሉንም ይወክላል ተብሎ ባይታሰብም የዳኞቻችን አጠቃላይ ሥነ ምግባርን ግን እንድንፈትሽ የሚጠቁም አጋጣሚ ነው።

ሌላኛው ጉዳይ በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ በነበረው ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ አልቢትር ለሚ ንጉሴ ሲዳማ ቡና በኋላ ላይ ጨዋታውን ያሸነፉባት ሆኖ የተመዘገበችው የፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠችበት ሂደት አወዛጋቢነት ነበር። ሳጥን ውስጥ ይገዙ ቦጋለ ላይ በረከት ወልደዮሐንስ ጥፋት ሰርቷል በሚል የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ከተለያየ የእይታ አድማስ የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት ፍፁም ተገቢ ያልነበረ ውሳኔ ነበር። በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ላይ የተሰጠውም የፍፁም ቅጣት ምት ክስተት በድጋሚ ሲታይ አበባየሁ አጪሶ የጎላ ንክኪ ሳይደረግበት መውደቁን ያሳያል። ይህንን ተከትሎ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ መክብብ ደገፉ የእንድሪስ ሰዒድን ምት ለማዳን ቀድሞ መስመሩን እንደለቀቀ ተስተውሏል። የጨዋታው አነጋጋሪነት በዚህ ሳያበቃ ይገዙ ቦጋለ በቢኒያም ገነቱ የተሰራበት የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ጥፋት በዝምታ ሊታለፍ ችሏል።

የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በዚህ ጨዋታ ላይ በታዩ ግድፈቶች መነሻም ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥናን በተመሳሳይ ከውድድሩ ሸኝቷል።

ውድድሩ ወደ ፍፃሜው እየቀረበ እንደመገኘቱ በተለይ በዚህ ወቅት ዳኝነቶች በተቻለ መጠን ከስህተት የፀዱ መሆን ይገባቸዋል። በመሆኑም አሁንም ዳኝነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዞ መፍትሄዎችን ይዞ መምጣት የግድ ይላል።

👉 የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች በሜዳ ተገኝተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ቡድን አባላት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በርከት ባሉ ጨዋታዎች ሜዳ ተገኝተው ጨዋታዎችን ሲከታተሉ ተመልክተናል።

ከዚህ ቀደም በሃዋሳ ፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ከተማ በተደረጉ ውድድሮች ጨዋታዎች ሲታደም የተመለከትነው እና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የአሰልጣኞች ቡድን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታውን ታድሟል።

ከቀጣይ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ለአህጉራዊ ውድድሮች ሲባል ሊጉ ከመቋረጡ አስቀድሞ አሰልጣኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ እጩዎቻቸውን ለመመልከት በሜዳ እንደተገኙ ይታመናል።